የሳላዲን የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝውውር ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል

ከወራት በፊት ከአልጄርያው ክለብ ኤምሲ አልጀርስ ጋር በፋ ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ ሆኖ የቆየው ሳላዲን ሰኢድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረሙ የማይቀር እየሆነ መጥቷል፡፡ ሳላ ከአልጄርያ መልስ ያለፉትን 4 ሳምንታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየ ሲሆን እስከቀጣዩ ሳምንት ድረስ ለፈረሰኞቹ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከክለቡ አካባቢ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የአሰልጣኝ ቡድኑ ሳላዲንን አጥብቆ የሚፈልግ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከቦርዱ መልካም ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል፡፡

በጉዳዩ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን የሰጠው ሳላዲን በበኩሉ ወኪሉ አሁንም ከዱባይ እና ግብፅ ክለቦች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ጠቅሶ ካልተሳካ ምርጫው ለፈረሰኞቹ ፊርማውን ማኖር እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

በአርባምንጩ ጨዋታ ብሪያን ኡሞኒ ለ3 ወራት ከሜዳ የሚያርቀውን ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ አሰልጣኝ ማርት ኑይ ሁነኛ አጥቂ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ2000-2002 የቅዱስ ጊዮርጊስን ማልያ የለበሰው ሳላ በፍጥነት ፊርማውን ያኖራል ተብሏል፡፡

ያጋሩ