“በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ 50ኛ ጎል በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል” አማኑኤል ገብረሚካኤል

አማኑኤል ገ/ሚካኤል በመቐለ 70 እንደርታ ማልያ ስላስቆጠረው 50ኛ ጎል ይናገራል።

በ2009 ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ወደ መቐለ አምርቶ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ እና ዐምና የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ ድርሻ የተወጣው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ዛሬ ደግሞ በመቐለ ቆይታው ሀምሳኛ ግቡን አስቆጥሯል።

ዛሴ ቡድኑ ወልዋሎን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው አማኑኤል ለመቐለ ሀምሳ ግብ ማስቆጠሩ ደስታ እንደፈጠረለት እና በቀጣይም ለክለቡ ያለውን ነገር ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል።

” ለክለቤ ሀምሳኛ ግቤ በማስቆጠሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ይህች ጎል በዚህ ወሳኝ ጨዋታ መሆኗ በጣም ደስ ብሎኛል። በዚ መጠን ለክለቤ ግብ ማስቆጠሬ እና ጎሏም የዚህ ወሳኝ የደርቢ ጨዋታ ማሸነፊያ መሆንዋ ደስታዬን ድርብ ያደርገዋል። በግል እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ማሳካት ትልቅ ታሪክ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከዚህ በፊት በደርቢው ጨዋታ ላይ ጎል አስቆጥሬ አላቅም ነበር፤ ዛሬ የመጀመርያ ግብ ማስቆጠሬም ደስ ብሎኛል” ብሏል።

ከዚ በተጨማሪ ተጫዋቹ ዘንድሮም የሊጉን ዋንጫ በድጋሚ ለማሸነፍ እንደሚጫወቱ ገልጿል። “እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ለዋንጫ ነው የምንጫወተው። በሊጉ መጀመርያ ላይ ትንሽ መቀዛቀዞች ነበሩ፤ አሁን ግን ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች አሸንፈን ነጥባችንን ከፍ አድርገናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ