ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በምዓም አናብስት አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የአምስተኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ ጨዋታን መቐለ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወደ ሊጉ የጣምራ መሪነት ተሸጋግሯል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በቅርቡ የዓለምአቀፉ ጣቢያ የሲኤንኤን /CNN/ የዓመቱ ጀግና ተብላ የተመረጠችው ፍሬወይኒ መብራህቱ በስታዲየም የገኘች ሲሆን ከደጋፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ሲዳማ ቡናን ካሸነፈው ስብስብ አሚን ነስሩ እና አሸናፊ ሀፍቱን በላውረንስ ኤድዋርድ እና ዳንኤል ደምሴ ተክተው ሲገቡ ወልዋሎዎችም ጅማን ከገጠመው ስብስብ ሚካኤል ለማና ሰመረ ሀፍታይን በካርሎስ ዳምጠው እና ፍቃዱ ደነቀ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

እጅግ በሚማርክ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታው ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና የመቐለዎች ሙሉ ብልጫ የታየበት ነበር። በጨዋታው መቐለዎች ከሌላው ግዜ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን ወልዋሎዎችም እንደ ባለፈው ጨዋታ ሁሉ ተገማቹ የማጥቃት አጨዋወታቸው ውጤታማ ሊያደርጋቸው አልቻለም።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው መቐለዎች የጨዋታው ኮከብ በነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም አማኑኤል ከርቀት ያደረጋት ሙከራ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ከሥዩም ተስፋዬ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ጎል በሀያ አራተኛው ደቂቃ ተገኝታለች። አማኑኤል ገብረሚካኤል በጠባብ አንግል አክርሮ የመታት ኳስም ወደ ግብነት ተቀይራ መቐለን መሪ ማድረግ ችላለች።

በጨዋታው በተጋጣሚያቸው ብልጫ የተወሰደባቸው ቢጫ ለባሾቹ ምንም እንኳ በርካታ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ካርሎስ ዳምጠው ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማለትን ኳስ ወደ ግብነት ያልቀየረው ወርቃማ ዕድል እና ጁንያስ ናንጂቡ እና ኢታሙና ኬይሙኔ በመልሶ ማጥቃት ሄደው ፊሊፕ ኦቮኖ ወጥቶ ያዳነው እንዲሁም በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ከረጅም ርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በአጓጊ ትእይንቶች ታጅቦ የተካሄደ ነበር። በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት መቐለዎች ሲሆኑ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ የተደረገ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል። ሙሉጌታ በተጨማሪም ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ መትቶ ዓብዱልዓዚዝ ኬታ እንደምንም ያዳነው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው የገቡት ወልዋሎዎችም በምስጋናው ወ/ዮሐንስ እና ሰመረ ሀፍታይ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ገናናው ረጋሳ ሳሙኤል ዮሐንስ ከመስመር ያሻማለትን መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት ኳስ እና ሰመረ ሀፍታይ የተመለሰውን ኳስ መትቶ ያደረገው ሙከራ ወልዋሎን የማታ ማታ አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

በጨዋታው መገባደጃ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው የወልዋሎው ግብ ጠባቂ አብዱላዚዝ ኬይታ ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ከዋናው ዳኛ ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በመቐለ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎ ባለበት በአስር ነጥብ ሲረጋ መቐለ ነጥቡን ወደ አስር ከፍ አድርጎ ከቢጫ ለባሾቹ ጋር በነጥብ ተስተካክሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ