የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂደው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ እና መከላከያ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። መዲና ዐወልም ሐት-ትሪክ በመስራት ደምቃ አምሽታለች።
በ9:00 የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ በነበረው የመጀመርያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ኳስ ከማንሸራሸር ባለፈ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩት በጥቂት አጋጣሚዎች ሲሆኑ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የአቃቂዋ ቤዛዊት ንጉሴ ከተከላካዮች አምልጣ በመውጣት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ሲመለስባት ሰላም ኃይሌ መትታ ወደ ውጪ የወጣው ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በአንፃራዊነት የተሻለ የነበረው ሁለኛወረ አጋማሽ እንደ መጀመርያው ሁሉ በርካታ ሙከራዎች ባይታዩበትም ጥሩ ፉክክር ተስተውሎበታል። በ60ኛው ደቂቃም የጨዋታው ብቸኛ ጎል ተቆጥሯል። ማህሌት ታደሰ ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀይሮ አቃቂ ቃሊቲን መሪ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ አቃቂዎች መሪነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሏቸው አጋጣሚዎች የፈጠሩ ሲሆን በ64ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ሲያመልጣት በድጋሚ በመምታት ቢሞክሩም ስርጉት ያዳነችው እንዲሁም ተቀይራ የገባችው ንግስት ኃይሉ ግብ ጠባቂዋን ብታልፍም ተከላካይ ደርሳ ያወጣችባት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በአዲስ አበባ በኩል ደግሞ 90ኛው ደቂቃ ምርትነሽ ዮሐንስ ሳጥን ውስጥ ወርቃማ ዕድል አግኝታ ያመከነችው ኳስ ቡድኗን አቻ ለማድረግ የቀረበች ነበረች።
በጨዋታው 78ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ከተማዋ ፍቅርተ ካሣ በሰራችው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብታለች።
11:00 ላይ የቀጠለው የመከላከያ እና ጌዴኦ ዲላ ጨዋታ በጦሩ 5-2 አሸናፊነት ተገባዷል። በፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ ጎል ለማስተናገድ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። ገና በአንደኛው ደቂቃ አጥቂዋ መዲና ዐወል ያስቆጠረችው ጎል መከላከያን ቀዳሚ አድርጓል። በጎሉ የተነቃቁት መከላከያዎች በ12ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ ፀጋ ንጉሴ አስቆጥራ ልዩነታቸውን አስፍተዋል።
ገና በጊዜ ጎሎች ያስተናገዱት ዲላዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በማድረግ ወደ መከላከያ የጎል ክልል የደረሱ ሲሆን በ21ኛው ደቂቃም ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ድንቅነሽ በቀለ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ለውጣ ልዩነቱን አጥብባለች።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በዲላ ሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት መከላከያዎች የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም መዲና ዐወል የመታችው ኳስ ቋሚውን ለትሞ ተመልሶበታል። ምንም እንኳን ጦሮቹ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያመክኑም ተጨማሪ ሁለት ጎሎችን በመጀመርያው አጋማሽ በማስቆጠር መሪነታቸውን አስፍተዋል። በ38ኛው ደቂቃ አረጋሽ ከልሳ ከመሐል ሜዳ የተጣለላትን ኳስ ከመስመር አጥብባ በመግባት ግብ ጠባቂዋን ጭምር አልፋ ስታስቆጥር በ43ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ መዲና ዐወል ወደ ጎልነት በመለወጥ በ4-1 ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ ከጎል ልዩነቱ መስፋት ጋር ጨዋታው በቀዝቃዛ ፉክክር የተካሄደ ሲሆን ዲላዎች የኳስ ቁጥጥሩ ላይ የተሻሉ ቢሆኑም መከላከያ የጎል እድል በመፍጠር እና ከጎሉ ፊት ስል በመሆን የተሻሉ ነበሩ። በ60ኛው ደቂቃም መዲና ዐወል ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ባስቆጠረችው ጎል ሐት-ትሪክ በመስራት የቡድኑን መሪነት አስፍታለች። መዲና ከቡድን አጋሯ ሄለን እሸቱ፣ ከባንኳ ሽታዬ ሲሳይ እና የአዳማዋ ሴናፍ ዋቁማ በመቀጠል ዘንንሮ ሐት-ትሪክ የሰራች አራተኛዋ ተጫዋች ሆናለች።
ከጎሉ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል የደረሱ ሲሆን በተለይም በ85 እና 87ኛው ደቂቃዎች ህይወት ረጉ እና መዲና ዐወል የጎሉ ብረት የመለሱባቸው ሙከራዎች ልዩነቱን ሊያሰፉ የሚችሉባቸው ነበሩ። በመጨረሻም ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ድንቅነሽ በቀለ ለዲላም ለራሷም ሁለተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ