ዓይናለም ኃይለ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል

በትናንትናው ዕለት ጉዳት አስተናግዶ ወደ ሆስፒታል የተወሰደው ዓይናለም ኃይለ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ትናንትና በተደረገው የትግራይ ደርቢ በተጨማሪ ሰዓት ላይ ከተጫዋች ጋር ተጋጭቶ በትከሻው አከባቢ ስብራት የገጠመው ተከላካዩ ጨዋታው ካለቀ በኃላ ወደ ሆስፒታል አምርቶ በቂ ህክምና ያገኘ ሲሆን ጉዳቱም ከሦስት እስከ ስድስት ሳምንታት ከሜዳ ሊያርቀው እንደሚችል ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ምርመራዎች የሚያደርገው ተጫዋቹ ከህክምናው በኃላ ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ይረጋገጣል ተብሏል።

ከዚ ቀደምም ጋናዊው የመሀል ተከላካይ አቼምፖንግ አሞስ በተመሳሳይ የጎን አጥንት ስብራት ያጡት ወልዋሎዎች በቀጣይ ሳምንት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ቀይ ካርድ ያየው ዓብዱልዓዚዝ ኬይታን ጨምሮ ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ያጣሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ