ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ ተከናውነዋል። በስምንቱ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በየጨዋታዎቹ ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ 3-4-3


ግብ ጠባቂ

ይድነቃቸው ኪዳኔ – ወልቂጤ ከተማ

በጉዳት መሰለፍ ባልቻለው ሶሆሆ ሜንሳህ ምትክ የገባው አንጋፋው ግብጠባቂ ይድነቃቸው ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ወላይታ ድቻን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ኳሶችን በማዳን ከሶዶ ስታዲየም ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲመለስ አስችሏል።

ተከላካዮች

ዳግም ንጉሴ – ወልቂጤ ከተማ

በተመሳሳይ ወልቂጤዎች ወላይታ ድቻን ባሸነፉበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ የተፈጠረባቸውን ጫና በመመከት ረገድ የወልቂጤን የመከላከል አደረጃጀት በመምራትና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የተሻለ የጨዋታ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል።

ዓይናለም ኃይለ – ወልዋሎ

አንጋፋው ተከላካይ በሳምንቱ ተጠባቂ የትግራይ ደርቢ ጨዋታ ለቡድኑ ባለውለታ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆኑም። ቡድኑ አንድ ለባዶ በተሸነፈበት ጨዋታ ውጤቱ እንዳይሰፋ በግሉ ከፍተኛ ተጋድሎን ሲያደርግ ውሏል።

ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና

በክረምቱ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ወንድሜነህ ቡድናቸው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ጎል አቻ በተለያየበት ጨዋታ ቡናን ኳስ መስርተው እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በዘለለ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አበርክቶ ነበረው።

አማካዮች

ጫላ ተሺታ – ወልቂጤ ከተማ

ወጣቱ የመስመር ተጫዋች በወልቂጤ ከተማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በድቻውም ጨዋታ ላይ ለቡድኑ ብቸኛዋን የማሸነፍፊያ ግብ ከማስቆጠር በዘለለ በጨዋታው ከመስመሮች እየተነሳ የወላይታ ድቻ ተከላካዮች ላይ ስጋት ሲፈጥር ውሏል።

ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ

ቡድኑ ምንም እንኳን በስተመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ግቦች አቻ ቢለያይም ሀብታሙ ተከስተ በግሉ ከተከላካዮች ቀርቦ ኳሶችን በመቀበልና በማደራጀት እንዲሁም ከፊቱ ለተሰለፉት ሁለት አማካዮች ጥሩ ጥሩ ኳሶችን በማቀበል የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል።

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

ዘንድሮ በፋሲል ተካልኝ ቡድን ውስጥ ወሳኝ ሚናን እየተወጣ የሚገኘው አማካዩ ፍቅረሚካኤል በሆሳዕናው ጨዋታ ላይ የሆሳዕናን አማካዮችን ከጨዋታ ውጭ ከማድረግ በዘለለ ቡድኑ በጨዋታው ካስቆጠራቸው ግቦች በአንዱ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ችሏል።

ያሬድ ከበደ – መቐለ 70 እንደርታ

በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተካተተ ሲሆን ቡድኑ ወልዋሎን ሲረታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ለነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም በተሰለፈበት የመስመር አማካይነት ሚና ጥሩ ግልጋሎትን ለቡድኑ አበርክቷል።

አጥቂዎች

ፍፁም ገብረማርያም – ሰበታ ከተማ

ታታሪው አጥቂ ፍፁም ቡድኑ በስተመጨረሻ ደቂቃዎች ከፋሲል አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሁለት ኳሶችን በግንባሩ በመግጨት ግብ ለማስቆጠር እየተቸገረ ለሚገኘው ቡድኑ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይቷል።

ማማዱ ሲዲቤ – ባህርዳር ከተማ

በክረምቱ ባህርዳርን የተቀላቀለው የተሟላው የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሲዲቤ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲካተት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በአዲሱ ቡድኑ አሁንም በአስደናቂ አጀማመሩ ቀጥሏል ፤ ለተለያዩ አይነት አጨዋወቶች የተመቸ የሆነው አጥቂው በሆሳዕናው ጨዋታ ለባህርዳር ከተማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ግልጋሎት ከመስጠት በዘለለ አንድ ግብን ማስቆጠር ችሏል።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – መቐለ 70 እንደርታ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንደ አምናው ሁሉ የመቐለዎች የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው አማኑኤል በትላንቱም ተጠባቂ ጨዋታ ላይ ወሳኝዋን የማሸነፊያ ግብ ከማስቆጠር በዘለለ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል፤ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲካተት እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ተጠባባቂዎች

ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባ ጅፋር)

ግርማ በቀለ (ሲዳማ ቡና)

አለልኝ አዘነ (ሀዋሳ ከተማ)

ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

ሀብታሙ ገዛኸኝ (ሲዳማ ቡና)

ሳሙኤል ዘሪሁን (ድሬዳዋ ከተማ)

ቢስማርክ አፒያ (ሀዲያ ሆሳዕና)

© ሶከር ኢትዮጵያ