የ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐበይት ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዳሜ ጅማሮውን አድርጎ ትላንትና ተጠናቋል፤ ድራማዊ ክስተት በተስተናገደበት ጨዋታ ፋሲል ከሰበታ ጋር ነጥብ ሲጋራ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ ለመጀመርያ ጊዜ ተሸንፏል። ሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማም ማሸነፍ ችለዋል። እንደተለመደው የዚህኛው ሳምንት ትኩረት ማዕከሎች በተከታዩ መልክ ቀርበዋል።


1) ክለብ ትኩረት

*በስተመጨረሻም ወደ ሜዳው የተመለሰው ጅማ ሦስት ነጥብ አሳክቷል

ዐምና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በጅማ ስታዲየም በተፈጠረ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሲያደርግ የነበረው ጅማ አባጅፋር ከቅጣት መልስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ከበርካታ የሜዳ ውጭ ሁነቶች ሲታመስ ለከረመው ቡድኑ በስተመጨረሻም ወደ ሜዳው መመለሱ ለቡድኑ የተሻለ ተስፋን የፈነጠቀ አጋጣሚ ሆኗል። ብዙ ጥያቄዎች ሲነሰቡት የነበረው የአሰልጣኝ ጳውሎስ ቡድን ስብስብ ከ5 ሳምንታት ጨዋታ በኋላ በ6 ነጥብ በ10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

*ሀዲያ ሆሳዕና እና አስከፊው የሊግ ጅማሮ

ሊጉን በአዲስ መልክ የተቀላቀለው ሀዲያ ሆሳዕና በ2008 የውድድር ዘመን ወደ ሊጉ በመጡበት አመት ወደ ከፍተኛ የሊግ የተመለሱበት አካሄድ ዘንድሮ እንዳይደገም ከአሁኑ ነገሮችን ማስተካከል ያለባቸው ይመስላል።

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከተቀላቀሉ ክለቦች እስካሁን ምንም ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ቡድኑ በ2 ነጥብ በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል፤ ምንም እንኳን ሊጉ ከተጀመረ ገና ጥቂት ሳምንታት ቢሆንም ቡድኑ በአዳማ ከተማ ዋንጫ ላይ ያሳየውን ተስፋ ሰጪ ጅማሮ በሊጉ መድረገም ተስኖታል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ቡድኑ በስብስብ ደረጃ በቀደሙት ጥቂት አመታት መቐለ 70 እንደርታ፣ ባህር ዳር ከተማና ጅማ አባጅፋር ወደ ሊጉ በመጡበት ዓመት የተሻለ የውድድር ጊዜያትን ካሳላፉ ቡድኖችን ጋር በተመጣጣኝ የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኝ የቡድን ስብስብ የያዘ ቢመስልም እስካሁን የሊጉን የውጤታማነት ጉዞ ቀመር ቡድኑ ለማግኘት ተቸግሮ ተስተውሏል።

ቡድኑ በ2008 መጥቶ በወረደበት የውድድር ዓመት በተለይ ነገሮች ከረፈደ ማለትም በሁለተኛው ዙር ቡድኑን ለማትረፍ ከተጫዋቾች ዝውውር ጀምሮ ከፍተኛ ጥረቶች ቢደረጉም ቡድኑ መትረፍ ሳይችል ቀርቷል። በተመሳሳይ ቡድኑ ዐምና ወደ ሊጉ ማለፉን ሲያረጋግጥ የቡድኑ አመራሮች የ2008 ተሞክሮን በመውሰድ ነገሮችን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ በገለፁት መሠረት ነገሮች መስመር ሳይስቱ ካሁኑ የእርምት እርምጃዎች መወሰድ ተገቢ ስለመሆኑ ፍንጮች እየታዩ ነው።

*አስደናቂው የሲዳማ ቡና የአጥቂዎች ጥምረት

በአዲስ ግደይ፣ ይገዙ ቦጋለና ሀብታሙ ገዛኸኝ የሚመራው የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር በዘንድሮው የውድድር ዘመን ብሩህ የውድድር ዘመን ጅማሮን እያደረጉ ይገኛል።

እጅግ ፈጣኖቹ ሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊ አጥቂዎች በሚዋልልና ለተቃራኒ ተከላካዮች አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኝን ክፍተት በማጥቃት ረገድ እስካሁን ወደር አልተገኘላቸውም። ምንም እንኳን ቡድኑ የእነዚህን አጥቂዎች አቅም ይበልጥ መጠቀም ከሚችልበት የጨዋታ መንገድ ውጭ በኳስ ቁጥጥር ለመጫወት በሚያደርጉት ጥረት የተነሳ እንጂ ከዚህ በላይ ውጤታማ መሆን በቻሉ ነበር።

ይህ ጥምረት ከዐምና ጀምሮ መሻሻሎችን እያሳያ ይገኛል። በተለይም የተለያዩ ተጫዋቾች ተሞክረው ውጤታማ መሆን በተሳናቸው የዘጠኝ ቁጥር ቦታ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከአምና ሁለተኛ ዙር ጀምሮ ባሳየው ተስፋ ሲጪ እንቅስቃሴ ለአስደናቂ የፊት ሶስትዮሽ ጥምረት ጎድሎ የነበረውን ስፍራ ዘንድሮ ይበልጥ የተሟላ ይመስላል።

*ፋሲል ከተማ በእጁ የገባውን ነጥብ አሳልፎ ሰጥቷል

በ5ኛ ሳምንት ፋሲል ከተማ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም አቅንቶ በቀድሞ አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ከሚመሩት ሰበታ ከተማዎች ጋር 3-3 በሆነ የአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል። እስከ 90ኛው ደቂቃ 3-1 እየመሩ የነበሩት ፋሲሎች በ90+1 እና በ90+3ኛው ደቂቃ በፍፁም ገ/ማርያምና አስቻለው ግርማ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች 3 አቻ ለመለያየት ተገደዋል።

*ድሬዳዋ ከተማና የተጫዋቾች ጉዳት

ደካማ የውድድር ዘመን ጅማሮን እያደረጉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁንም በጉዳት መታመሳቸውን ቀጥለዋል።

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ለማጣት ተገደዋል፤ ገና ከወዲሁ 11 ግቦችን ያስተናገዱት ድሬዳዎች ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ወሳኝ የመሀል ተከላካያቸውን በረከት ሳሙኤልና ወሳኙን የመስመር አጥቂ ሳሙኤል ዘሪሁንን እንዲሁ በጉዳት ለማጣት ተገደዋል።

ያሬድ ሀሰን፣ ምንያህል ተሾመ እና ረመዳን ናስር በጉዳት ላጡት ድሬዳዎች በተመሳሳይ የእነዚሁን የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋቾች ግልጋሎት አለማግኘት ቡድን ይበልጥ ሊያሳሳው እንደሚችል ይገመታል።

*ቅዱስ ጊዮርጊስ በስተመጨረሻም ግብ አስተናግዷል

እስከ 4ኛ ሳምንት ድረስ ምንም ግብ ሳያስተናግዱ የቆዩት ፈረሰኞቹ በስተመጨረሻም በ5ኛ ሳምንት መረባቸውን አስደፍረዋል።

2) ተጫዋቾች ትኩረት

*ጫላ ተሺታ በወልቂጤ ቤት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኗል

ወጣቱ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ እምብዛም ስኬታማ ካልነበረው የሲዳማ ቡናው ቆይታ መጠናቀቅ በኋላ በደግዓረግ ይግዛው የሚመሩትን ወልቂጤ ከተማን ከተቀላቀለ በኃላ በሊጉ ጥሩ ጅማሮን እያደረገ ይገኛል፤ የመስመር አጥቂውም በሳምንቱ መጨረሻ ወልቂጤ ከሜዳቸው ውጭ ተጉዘው ከአስቸጋሪው የወላይታ ሶዶ ስታዲየም ሙሉ ሶሶት ነጥብ ይዘው ሲመለሱ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ተጫዋቹ በተመሳሳይ ቡድኑ ፋሲል ከተማን በረታበት ጨዋታ እንዲሁ ለተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ፈታና ሆኖ ውሏል። መነሻውን ከተለጠጠ አቋቋም በማድረግ በአስደናቂ ፍጥነት ተጫዋቾችን ቀንሶ ሳጥን ውስጥ የሚገባው ይህ ተጫዋች ለወልቂጤዎች በዘንድሮው ዓመት ውጤታማነታቸው ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

*የአማኑኤል 50ኛ ግብ ለመቐለ

2009 ክረምት መቐለን የተቀላቀለው አማኑኤል ትላንት በትግራይ ደርቢ ያስቆጠራት ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ በመቐለ መለያ ያስቆጠራት 50ኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች። አማኑኤል ምንም እንኳን በጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ካለፉት ዓመታት አንፃር እምብዛም ቢሆንም በአምስት ጨዋታ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ውጤታማነቱን ይዞ ቀጥሏል።

3) ድህረ ጨዋታ አስተያየት

*የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ቡድኖች ሊመዘኑበት ስለሚገባው መመዘኛ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“አንድን ነገር ተግባራዊ የምታደርገው በአንድ ሁለት ጨዋታ አይደለም ጊዜ ይፈልጋል። አንድ ቡድን መለካት ያለበት በማሸነፍ ብቻ መሆን የለበትም ፤ አንዱ መለኪያ ማሸነፍ ቢሆንም በተጋጣሚህ ቡድን ላይ የምትወስደው ብልጫ መታይት አለበት። ስለዚህ በንፅፅር ሲታይ ከተጋጣሚ የተሻልን ነበር።”

*የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ ስለ ከፍተኛ ሊጉና ፕሪምየር ሊጉ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል

“እኔ ሊጉ ላይ ምንም አይነት ለውጥ አላየሁም የኢትዮጽያ ሊጎች በሙሉ አንድ ኩሬ ውስጥ ነው ያሉት ፤እኔ አምና በከፍተኛ ሊግ ነበርኩኝ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስመጣም ምንም ልዩነት አላየሁም፤ ሁለቱም ያው ናቸው። የዘንድሮ ሊግ በመሠረታዊነት ሁለት ነገሮች ተሻሽለዋል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው ነገር ሊጉ ላይ የትኛውም ሜዳ ላይ ሁሉም ቡድኖች ወጤቱን በፀጋ ተቀብሎ ነው የሚወጡት ፤ ሁለተኛው ነገር አብዛኛው ቡድኖች ኳስ ለመጫወት ይሞክራሉ፤ ይሄ የሚያስደስት ነገር ነው።”

*የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሶዶ ስታዲየም ላይ መሻሻሎች ስለመኖራቸው ምስክርነት ሰጥተዋል

“አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ለዛሬው ውጤታችን ማማር የድቻ ሜዳ ትልቁን አስተዋዕኦ አድርጎልናል ፤ከዚህ በፊት ሲተች እሰማው የነበረውን ሜዳ በዚህ አጭር ጊዜ አሻሽለው በማቅረባቸው በእውነት ሊመሰገኑ ይገባል።”

* የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ቡድኑ ለተጫዋቾች ደሞዝ አልመክፈሉ

“ባለፈው የነበረው ችግር በተወሰነ መልኩ ተቀርፏል። በቀጣይ ቀናትም ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፍ ነው ስራ አስፈፃሚው ተወያይቶ መፍትሔ ያስቀመጠው። ይህ ጉዳይ በቡድኑ ውጤት ላይ ብዙም ተፅዕኖ የሚያመጣ አይደለም።”

4) በግብ የተንበሸበሹ ጨዋታዎች

ለወትሮም ቢሆን ባለሜዳ ቡድን ለማሸነፍ እንዲሁም እንግዳው ቡድን አለመሸነፍን ተቀዳሚ አማራጫቸው በማድረግ በሁለት የተለያዩ ፅንፎች በመሆን የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሊጉ መገለጫ ባህሪ እስኪመስል ድረስ ያለ ግብ በአቻ የሚጠናቀቁ እንዲሁም በጠባብ ልዩነት የሚያልቁ ጨዋታዎች በሊጉ የሳምንት ሳምንት ጉዞ ውስጥ የተለመዱ አይቀሬ ክስተቶች ናቸው።

ዘንድሮ ግን እስካሁን በተደረጉት የ5 ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ከሜዳቸው ውጭም ለማሸነፍ የሚጫወቱ ቡድኖችን እየተመለከትን እንገኛለን። ለአብነትም በዚህ ሳምንት የተካሄዱት የሰበታና ፋሲል (3-3) እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናና ባህርዳር (2-2) ጨዋታን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ (2-2)ለዚህ ሀሳብ በማሳያነት መቅረብ የሚችሉ ውጤቶች ናቸው።

በቀጣይ ይህ ሂደት የሚቀጥል ከሆነ ተገማች ለነበረውና በሜዳ ላይ የሚጫወቱ ቡድኖች መገለጫው ለሆነው ሊጋችን ጤናማ የሆነ የፉክክር ሚዛንን በመፍጠር ሊጉን አዲስ መልክ ያላብሰዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

5) የሜዳ ላይ የህክምና እርዳታ

የገንዘብ ችግር በሌለበት በሀገራችን እግርኳስ ትኩረት ከተነፈጉ ነገርግን ለስፖርቱ መሠረታዊ ከሆነ ነገሮች አንዱ የሆነው የስፖርት ህክምና ጉዳይ አንዱ ነው።

ለዚህ ጉዳይ መነሻ የሆነው ሁነት ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ 60ኛው ደቂቃ ሁለት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ጉዳት ገጥሟቸው በተመሳሳይ ቅፅበት በወደቁበት ወቅት የሲዳማ ቡናው ወጌሻ የህክምና እርዳታ ለመስጠት በገባበት ወቅት ለሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የሀዋሳው ከተማ የህክምና ባለሙያ እርዳታ ያደረገበት ሂደት ከሰብዓዊነት አንፃር የሚበረታታ ቢሆንም የቡድኖቻችንን ክፍተት በግልፅ የሚጠቁም ሆኖ አልፏል።

በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፉ ክለቦች ከኢትዮጵያ ቡና በስተቀር ቢያንስ በጨዋታ ቀን ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ያለው ቡድን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይደለም። ጉዳዩ ከብዛታቸው ብቻ ሳይሆን በህክምናው ሆነ ተዛማጅ ከሆኑ የሙያ ዘርፎች ሙያተኞችን በማምጣት የተዋቀረ የህክምና ቡድን ማዋቀሩ ቢሆንም በአብዛኛዎቹ የሊጉ ክለቦች ላይ የሚገኙት ባለሙያዎች የብቃት ደረጃ ሆነ በጨዋታ ቀን ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ይዘዋቸው የሚገቡት የመርጃ ቁሶች ላይም እንዲሁ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ቡድኖች እንደ ነገሩ የህክምና ባለሙያ በሚል አንድ ባለሙያ ከመያዝ በዘለለ አንድ ክለብ ሊያሟላ ከሚገባውና በቡድን ዋና ዶክተር የሚመራው የህክምና ቡድን ውስጥ 6 ብሎም ከዛ የበለጡ የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የተዋቀረ የህክምና ቡድን ማዋቀር ምንም እንኳን በአርቆ አሳቢነትና ከዘመናዊ እግርኳስ ለተራራቀው የእግርኳስ አመራሮች ጉዳዩ የቅንጦት አካሄድ ቢመስልም በውጤትና የቡድን ብቃት ከሚኖረው ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አንፃር ቡድኖች በዚህ ጉዳይ በትኩረት መስራት ይገባቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ