የውድድር ኮሚቴ አዲስ በዘረጋው ሥርዓት መሠረት ከቅጣት አስቀድሞ በዕርምት ሊያስተካክሉ ይገባቸዋል ካላቸው የክለብ አመራሮች ጋር በትናትናው ዕለት ውይይት አደረገ።
የፋሲል ከነማ ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተለይ በግል ፌስቡክ ገፃቸው ላይ በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ለጨዋታ ምቹ እንዳልነበረ የግል አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ እና ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል ደግሞ የስሑል ሽረ የቡድን አባላት ምዑዝ ኃይለ ሚካኤል (የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ)፣ መብራህቶም ፍስሀ(ም/አሰልጣኝ) እና በረከት ገብረመድህን(ቴክኒክ ዳሬክተር) የውድድር ኮሚቴ ሊያናግራቸው ቀጠሮ መያዙን መዘገባችን ይታወቃል።
በትናትናው ዕለት ኮሚቴው ግለሰቦቹን በአዲስ አበባ ስታዲየም በተናጥል ያናገራቸው ሲሆን ሁሉም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በወቅቱ የተደረገው ነገር ተገቢ እንዳልሆነ የጋራ መግባባት ደርሰዋል። በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ዕርምት መውሰዳቸውን በመግለፅ በጥሩ መግባባት ውይይቱ ተጠናቋል።
ከዚህ ቀደም ይሰራበት ከነበረው አሰራር በተለየ መንገድ ለውጥ ያደረገው አዲሱ የሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ ጥፋቶች ሲፈፀሙ በቀጥታ ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ለቅጣት ውሳኔ ከመላኩ በፊት አስቀድሞ በምክር እና በተግሳፅ በማናገር ስህተቶች እንዲታረሙ የሄደበት መንገድ ተገቢነቱ እየተገለፀ ሲገኝ የዲሲፕሊን ኮሚቴን ስራንም ማቅለሉ እየተነሳ ይገኛል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት እስከ አምስተኛ ሳምንት ድረስ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በቀይ ካርድ አልያም የቢጫ ማስጠንቃቂያ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔዎች ከመወሰኑ በቀር እስካሁን ከፍተኛ ቅጣት አላስተላለፈም።
© ሶከር ኢትዮጵያ