የፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንትን የምንዘጋው እንደተለመደው በሳምንቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች ይሆናል።

ጎል

– በአምስተኛ ሳምንት በአጠቃላይ 21 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች ጋር ተመሳሳይ ቁጥር ነው።

– በዚህ ሳምንት አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ጎል ሳይቆጠር ተጠናቋል። ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ብቸኛው ጎል ያልተስናገደበት ጨዋታ ነው።

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት 21 ጎሎች በ20 የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። ይህም ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪነት የተሳተፉበት ሆኖ አልፏል።

– ጎል ካስቆጠሩ 20 ተጫዋቾች መካከል 8 ጎሎች በመስመር፣ በተመሳሳይ 8 ጎሎች በመሐል አጥቂዎች፣ 2 ጎሎች በአማካዮች እንዲሁም 3 ጎሎች ከተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል።

– ፍፁም ገብረማርያም ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግብ ቀሪዎቹ 19 ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከ21 ጎሎች መካከል 19 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ እና ከተሻሙ ኳሶች (ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምት) ሲቆጠሩ ቀሪዎቹ 2 ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኘ ነው።

– ከዚህ ሳምንት ጎሎች መካከል 17ቱ በእግር ተመትተው የተቆጠሩ ናቸው። አራት ጎሎች ደግሞ በጭንቅላት ተገጭተው የተቆጠሩ ናቸው።

– ለተቆጠሩ ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል ረገድ 17 ተጫዋቾች ተሳትፈዋል። ቀሪዎቹ በፍፁም ቅጣት ምት ወይም ከተቃራኒ ተጫዋቾች ተነጥቀው የተቆጠሩ ናቸው።

– ከ21 ጎሎች መካከል ስድስት ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ሲቆጠሩ 15 ጎሎች የሳጥን ውስጥ ውጤቶች ናቸው።

የመጀመርያዎቹ

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ የመጀመርያ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ጅማ አባ ጅፋር የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል። ፈረሰኞቹ በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግባቸውን ያስደፈሩትም በዚህ ሳምንት ነው። ወልቂጤ ከተማ ደግሞ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን አሳክቷል።

ማሸነፍ የተሳነው ሆሳዕና

በሊጉ እስካሁን ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ብቸኛ ቡድን ሀዲያ ሆሳዕና ነው። ከአምስቱ ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ሲያስተናግድ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

ካርዶች

– በዚህ ሳምንት ከባለፈው ጋር ሲነፃጰር ዝቅ ያለ ቢጫ ካርድ ተመዟል። 29 ቢጫ እና አንድ ቀይ (ሁለተኛ ቢጫ) ካርዶች የተመዘዙት ይህ ሳምንት በከአራተኛው (37) እና ሁለተኛው ሳምንት (35) ቀጥሎ ሦስተኛው ነው።

– በጅማ አባ ጅፋር (4 ቢጫ) እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (3 ቢጫ) መካከል የተደረገው ጨዋታ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበበት ሲሆን የድሬዳዋ እና ቡና፣ የሀዋሳ እና ሲዳማ እንዲሁም የሰበታ እና ፋሲል ጨዋታ በሁለት ካርዶች ዝቅተኛው ቢጫ ካርድ የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ