የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ የሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” ክፍሌ ቦልተናን ይዞ ቀርቧል። በዛሬው የክፍል 1 መሰናዷችንም የክፍሌ የአሰልጣኝነት ጅማሮን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።
በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ የተመራው የ1985ቱ መብራት ኃይል ወሳኝ ተጫዋች ነበርክ፡፡ ይህ ቡድን በወቅቱ የሊግና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አንስቷል፡፡ እስቲ ብዙም ስላልተነገረላቸው አሰልጣኝ ወንድማገኝ አበርክቶ እናውሳ፡፡
★ በመጀመሪያ ያን ቡድን የሰበሰበው ጋሽ ሰውነት ነበር፡፡ የተወሰንን ተጫዋቾች ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ግብጽ ሄደን ከጠፋን በኋላ ተይዘን ወደ እዚህ መጣን፡፡ ከቡና ገበያ፣ መብራት ኃይል፣ እርሻ ሰብልና ከሌሎች የድርጅት ክለቦች ተመርጠው የነበሩት ተጫዋቾች ወደ ቋሚ ስራቸው ተመለሱ፡፡ እኔ ግን እዚህ ስንመጣ ጦሩ ፈርሶ ጠበቀኝና አንድ ዓመት ያለ ሥራ ተቀመጥኩ፡፡ ስለዚህ ቋሚ ሥራ የሚሰጥ ክለብ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ስታዲየም አካባቢ ጋሽ ሰውነት ቢሻውን አገኘሁትና ተነጋገርን፤ የመብራት ኃይል ዝግጅት በሶደሬ ይካሄድ ነበር፡፡ ከዚያ እኔም ቡድኑን ተቀላቀልኩ፡፡ ስብስቡ የሚገርም ብቃት ነበረው፤ በምን ምክንያት እንደሆነ ባላውቅም ጋሽ ሰውነት ቢሻው ለቆ ወጣ፡፡ ያኔ አቶ ወንድማገኝ ከበደ የክለቡ ቴክኒክ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ለበርካታ ዓመታት በበረኝነት ይጫወት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚያ ቡድኑን እርሱ ያዘው፡፡ እጅግ ጠንካራ ቡድን አደረገን፤ ስብስቡ ውስጥ ለብሄራዊ ቡድን የሚጫወቱ እነ ሸዋንግዛው፣ ክፍሉና ዳንኤልን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ተከተዋል፡፡ በእርግጥ ኋላ ላይ መብራት ኃይል ሲዳከም ወደ አሜሪካ ሄደዋል፡፡ ከታች ደግሞ እነ ተስፊቲን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች አደጉ፡፡ ወንድማገኝ በዲሲፕሊን ላይ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ ሥርዓት ያስከብራል፡፡ በወቅቱ አንዳንዶቻችን መዝናናት እናበዛ ነበርና ሜዳ ላይ እስከ መደባደብ በመድረስ ሥርዓት ያስይዘን ነበር፡፡ ጠንካራ ልምምድ ይሰጠናል፡፡ ከዚህ ውጪ ወንድማገኝ ክፋት የሚባል ነገር የሌለው በጣም የዋህ ሰው ነው፡፡ አሁን ተቀጥቶህና ተጣልቶህ፥ ትንሽ ቆይቶ አብሮህ ሲስቅ ታገኘዋለህ፡፡ አንድ ጊዜ እኔና በለጠ ወዳጆን ክፍል ውስጥ ያጣናል፤ እኔ ከኤልያስ ጁሐር ጋር አንድ ክፍል ነበር የምጋራው፡፡ ለካ ወንድማገኝ ጠዋት ቁርስ ላይ እየጠበቀን ኖሯል፡፡ እኔ ሄድኩና “እሺ ወንዴ!” ብዬው ሰላምታ ስሰጠው በቀጥታ በጥፊ ተቀበለኝ፡፡ ወንድማገኝ ለውጤታማነትና ለሥርዓት <Aggressive> ነው፡፡ ቢሆንም ጥፋታችንን ወዲያው ይረሳልን ስለነበር ማንም ተጫዋች ቂም እርሱ ላይ አይዝበትም፡፡ በዚህ መልኩ ትልቅ ቡድን መሥራት ቻለ፡፡ ከተመሰረተ ጀምሮ ለሰላሣ ዓመታት ያህል ከጥሎ ማለፍ ዋንጫ ውጪ አንስቶ የማያውቀው መብራት ኃይል በወንድማገኝ ከበደ አማካኝነት የዙሩን ውድድር ማሸነፍ ቻለ፡፡ እንግዲህ ያ ትልቅ ስኬት የወንድማገኝ ከበደ ነው፡፡ እንደማስታውሰው በመጨረሻው ጨዋታ ከቡና ጋር ተፋጠን ነው የዙሩን ውድድር ያሸነፍነው፡፡ እንዲያውም ገብረኪዳን ነጋሽ (ጋምብሬ) ቡናዎች ከመስመር ሲያጠቁ አብዛኞቹ ኳሶች ከእርሱ የሚነሱ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ቡና እኛን 2-0 ማሸነፍ ይጠበቅበት ነበር፡፡ እኛ ቀድመን ሁለት አገባን፥ እነርሱም እንዲሁ አከታትለው ሁለት አስቆጠሩ፤ 2-2 አቻ ወጣንና ዋንጫውን ወሰድን፡፡ የጥሎ ማለፉን ደግሞ ጊዮርጊስን 3-1 ረተን ዋንጫ አነሳን፡፡ በዚያ ስኬታማ ቡድን ግንባታ ላይ የወንድማገኝ ከበደ ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ከዓመት በኋላ ተበተነ፡፡
የአሰልጣኝነት ሙያ አጀማመርህን ተርክልን?
★ አሰልጣኝነት የጀመርኩት በመብራት ኃይል የ<C> ቡድን ነው፡፡ ከዚያ በፊት ለአስራ ሁለት ዓመታት ውጤታማ በነበሩት የጦሩ እና መብራት ኃይል ቡድኖች በተጫዋችነት ቆይቻለሁ፡፡ አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎቱና ሐሳቡ አልነበረኝም፡፡ ያኔ የነበረው ልማድ ኳስ ካቆሙ በኋላ ወደ ቢሮ ሥራ መግባት ነው፡፡ በ1990 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ሲጀመር አርባ ለምንሆን የቀድሞ ተጫዋቾች ኮርስ ሲሰጥ እኔም ተሳተፍኩ፡፡ ፈተናውን ወስጄ አለፍኩና የአየር ጤናን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ፕሮጀክት በአሰልጣኝነት ተረከብኩ፡፡ ከፕሮጀክቱ ወደ ላይ የሚያድጉ ብዙ ተጫዋቾች ተገኙ፡፡ በዚህም ሳቢያ በተመሳሳይ የዕድሜ እርከን የተዘጋጀውን የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ወደ ሐረር ይዤ የመሄድ አጋጣሚ ተፈጠረልኝ፡፡ በተጓዳኝ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በማውጣት የሚታወቀው አሰልጣኝ ቢረጋ (ነፍስ ይማር፡፡) ሲያርፍ የመብራት ኃይል <C> ቡድን አሰልጣኝነት ለእኔ ተሰጠኝ፡፡ እኔም የክለቡን ባህል ለማስቀጠል ጣርኩና ብዙ ተጫዋቾች ማፍራት ቻልኩ፡፡ እንዲያውም ያኔ ከ<C> ቡድን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን የሚያድጉ ልጆች ነበሩ፡፡ ዋናው የመብራት ኃይል ቡድን ወደ መልካ ዋከና ባመራበት ወቅት ” የአንተ ተጫዋቾች ብዙ ስለሆኑ እንደ ሶስተኛ አሰልጣኝ ሆነህ አብረኸን ትጓዛለህ፡፡” ተባልኩና ለዝግጅት አብሬ የመሄድ ዕድል አገኘሁ፡፡ ስለዚህም በ1990 የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን በሆነው ቡድን ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ተሳትፌያለሁ፡፡ ከጊዜያት በኋላ የተጫዋቾች አመራረጥ ሒደቱ ብዙም አልመች አለኝ፡፡ ከሶስት ሺህ ልጆች በላይ በቢሮ መዝግቦ በሜዳ ላይ ጥሩ ተጫዋች ለማግኘት መሞከሩን አልወደድኩትም፡፡ ያን ጊዜ እንደዛሬው የሜዳ ችግር አልነበረም፡፡ እኔ ደግሞ ተጫዋቾችን በየሜዳው መፈለጉን እወዳለሁ፡፡ሽሮሜዳ፣ ፒያሳ፣ አፋርሳና ሌሎችም ቦታዎች እየሄድኩ እነርሱ ሲጫወቱ ተመልክቼ መመልመሉን ነበር የምመርጠው፡፡ በየሰፈሩ የሚገኙ ልጆች በነጻነት ስለሚጫወቱ ተሰጥዖአቸውን ማውጣት ይችላሉ፡፡ ይህ አይነቱን አሰራር ከምዝገባው ጋር በማዋሃድ መስራቱን አምንበት ነበር፡፡ ለምሳሌ፦ እድሉ ደረጄን በዚህ መንገድ ፒያሳ ማዘጋጃ ሜዳ ነው ያገኘሁት፡፡ ከሶስት ዓመት የመብራት ኃይል ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር በዚሁ የምልመላ አካሄድ ጉዳይ አለመግባባት ላይ ደረስን፤ ” ተጫዋቾች ምዝገባ ሒድ!” ስባልም ፍላጎት አጣሁ፡፡ ከዚያ መብራት ኃይልን ለቀቅሁ፤ በድርጅቱ ግን ቋሚ ስራዬን መሥራቴን ቀጠልኩ፡፡
ቋሚ ሥራህ በምን ሙያ ላይ ነበር?
★ እኛ’ኮ ብዙም አልተማርንም፡፡ አብዛኛው ጊዜያችንን ኳስ ተጫውተን ነው ያሳለፍነው፡፡ በእኛ ጊዜ ከኳስ ተጫዋችነት ህይወት በኋላ አማራጫችን ወይ ወደ ውጭ መጥፋት አልያም በድርጅቶች ውስጥ ቋሚ ሥራ ማግኘት ነበር፡፡ የፊርማ ገንዘብ እኮ የመጣው አሁን ነው፡፡ ቀጣይ ህይወትህ ጥሩ እንዲሆን ያኔ እንደምንም ብለህ ብሄራዊ ቡድን ተመርጠህ ለመጥፋት ትጥራለህ፡፡ በመብራት ኃይል ስንጫወት የኪስ ገንዘብ መጠኑ መቶ ሃምሳ ብር ብቻ ነበር የሚሰጠን፡፡ ስለዚህ ለቀጣዩ ህይወታችን የምንጫወትበት ክለብ ቋሚ ሥራ ይሰጠናል፡፡ እኔም በመብራት ኃይል መዝገብ ቤት ውስጥ ምሰሶ መንከሪያ ክፍል እቀመጣለሁ፤ እሱንም ለመስራት ትምህርት ያስፈልግ ነበር፡፡ አሁን አሁን ገንዘቡ ሲመጣ መጥፋቱ ቀርቷል፡፡
ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ በአንተ የእግርኳስ አሰልጣኝነት ጅማሮ ስላሳደሩት ተጽዕኖ አዘወትረህ የምትሰጠው ምስክርነት አለ፡፡ የጋሽ ሐጎስን ውለታ አስታውሰን፡፡
★ ጋሽ ሐጎስ እውነተኛ ሰው ነበሩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሌሎች አሰልጣኞች ላይ የሚታየው የመለዋወጥ ባህርይ እርሳቸው ጋር የለም፡፡ ቀጥታ የሚሄዱ ንጹህ ሰው ናቸው፡፡ ሁላችንም እርሳቸውን እንደ አባት ነው የምናያቸው፡፡ የቀድሞውን እግርኳስ የተከታተለ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋሽ ሐጎስ በአየር ኃይል የሰሩትን በጣም ፈጣን ጨዋታ የሚያደርግ ቡድን ያውቃል፡፡ እርሳቸው ወደ መብራት ኃይል ሲመጡ በስልጠና ዘመናቸው በጣም እናከብራቸው ነበር፡፡ በተጫዋች አያያዛቸው ደግሞ ልዩ ሆነው አገኘናቸው፡፡ ተጫዋቾችን በቅንነት ይይዛሉ፡፡ እኔ የጦሩ ተጫዋች ሆኜ፥ እርሳቸው ደግሞ በአየር ኃይል አሰልጣኝ ሳሉ ተቃራኒ ሆነን በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ጦርነት ነው የሚመስለው፤ በተለይ የማታው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያውቁኝ ነበርና መብራት ኃይል ሲመጡ እኔ ቢሮ ቁጭ ብዬ ስውል አይተው አዘኑ፡፡ ያው ለረዥም ዓመታት እግርኳስ ተጫውተህ መጨረሻ ላይ ብቁ ባልሆንክበት ሙያ ቢሮ ለመሥራት መቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ የምሰራበት ቢሮና የክለቡ ስፖርት ጽ/ቤት ጎን ለጎን በመሆኑ እርሳቸውን በተደጋጋሚ የመገናኘት አጋጣሚ አገኘሁ፡፡ እርሳቸው ለእኔ ጥሩ አመለካከት ነበራቸው፡፡ ምናልባት ቢሮዬ ሌላ ቦታ ቢሆን ኖሮ ይሄ ዕድል ላይፈጠር ይችል ይሆናል፥ እርሳቸውም ላያስታውሱኝ ይችላሉ፡፡ አንድ ቀን ከጋሽ ሐጎስ ጋር ቢሮ አካባቢ ስናወራ ” ብዙ ተጫውተሃል፤ አዕምሮህም ለ<Coaching> ጥሩ ነው፡፡ ለምን የአሰልጣኝነት ኮርስ አትወስድም?” አሉኝ፡፡ እኔም ‘የመማር ዕድሉን ካገኘሁ እወስዳለሁ፡፡’ አልኳቸው፡፡ ከዚያ እንድማር ያበረታቱኝ ጀመር፡፡ እኔም የፕሮጀክት ኮርስ ወሰድኩ፤ ቆየሁና አንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ኮርስም ተማርሁ፡፡ እንደገና ደግሞ ቆይቼ በጊዮን ሆቴል የተሰጠው የካፍና የፊፋ ኮርሶች ላይም መካፈል ቻልኩ፡፡ ጋሽ ሐጎስ የተለዩ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ ማንም አሰልጣኝ የማያደርገውን ያደርጋሉ፡፡ እኛ የ<C> ቡድን ይዘን ስናሰራ መጥተው ያያሉ፡፡ እኔ ‘እነዚህ ተጫዋቾች ይደጉ፡፡’ ሳልል ጋሽ ሐጎስ በራሳቸው ” እገሌን፣ እገሌን፣ እገሌን፣… ላካቸው፡፡” ይሉና አስርና አስራ አምስት የ<C>ቡድን ወጣቶችን እያስጠሩ ከዋናው ቡድን ጋር ለዝግጅት ይዘዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ከዚያ በእርሳቸው የአካል ብቃት፣ ቴክኒክና የአዕምሮ ብስለት መስፈርት ብቁ ሆነው የተገኙትን ያሳድጋሉ፡፡ እርሳቸው በሁሉም ተጫዋቾች የሚከበሩ የተለየ <Quality> ያላቸው አሰልጣኝ ናቸው፡፡ እስቲ አሁን የየትኛው ክለብ አሰልጣኝ ነው የ<C> እና የ<B> ቡድን ጨዋታዎችን እየሄደ የሚያየው? ሁላችንም ለክለብ ስንቀጠር በኮንትራታችን ላይ “ይህን አይነት ውጤት አመጣለሁ፡፡” ብለን እንጂ የቋሚነት ሥሜት ተሰምቶን አንሰራም፡፡ አንዳንዴ ክለቦች የሚጎዱት ለዚህ ይመስለኛል፡፡ የክለቡ ቋሚ ሰው እንደሆንክ እያሰብክ ስትሰራ ታችም እየወረድክ ታዳጊዎችን በማየት አስተዋጽኦ ታደርጋለህ፡፡ ስትለቅም መሰረት ጥለህ ትወጣለህ፡፡ ብዙውን ጊዜ እኛ የምናስበው የምናሸንፈውን የጨዋታ ብዛት፣ ኮንትራታችንን እና የራሳችንን ህይወት ነው፡፡ ጋሽ ሐጎስ ግን ታች እየወረዱ <B> እና <C> ቡድን ያያሉ፡፡ እኔ ከምሰራበት ከ<C> ቡድን ደግሞ ብዙ ልጆችን ለላይኛው ቡድን አብቅተዋል፡፡ እርሳቸው በመብራት ኃይል የሰሩትን ማንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚረሳው አይደለም፡፡ በተከታታይ ዋንጫ የወሰዱ ታዳጊ ተጫዋቾችን ለሃገሪቱ ወጣት ብሄራዊ ቡድን የሚያፈሩ ነበሩ፡፡ ጋሽ ሐጎስ ሁሉንም ያዳምጣሉ፤ እኛንም ያሳትፋሉ፡፡ እርሳቸው የተለዩ ነበሩ፡፡ ለእኔም ለሌላውም ያበረከቱት አስተዋፅኦ እኔ ከምናገረውም በላይ ነው፡፡
አንተ ታሰለጥን በነበረው የ<C> ቡድን ያለፉና ለዋናው የመብራት ኃይል ቡድን በትልቅ ደረጃ መጫወት የቻሉ ተጫዋቾችን አስታውሰን፡፡
★ ብዙነህ ወርቁ፣ ታምራት አበበ፣ ዮናስ ገ/ሚካኤል፣ አለማየሁ ዲሳሳ፣ ኃይሉ አድማሱ፣ መስፍን አሰፋ (ቻይና)… የሚገርመው እነዚህ ተጫዋቾች ከ<C> በቀጥታ ያደጉ ናቸው፡፡
የቴክኒክ ሥልጠና ላይ የማተኮር ዝንባሌ ነው ያለህ?
★ እኔ የእግርኳሱ <Art> ይመቸኛል፡፡ ጥበቡን እወዳለሁ፡፡ በቃ የሚጫወት ቡድን ደስ ይለኛል፡፡ በፊት <C> ቡድን ሳሰለጥን ተጫዋቾቼ ዋንጫ ቢያሸንፉም እኔ ይበልጥ የሚያረካኝ አጨዋወታቸው ነበር፡፡ <Triangle> እየሰሩ ሲቀባበሉ ሳይ እደሰታለሁ፡፡ አሸንፈን እንኳ ‘ ዛሬ እንቅስቃሴያችሁ ምንም አልጣመኝም፡፡’ እላቸዋለሁ፡፡ ተጫዋቾቹም ይህ ባህርዬን ያውቃሉ፡፡ ሶስቱንም ዓመት በታዳጊዎች ውድድር የአዲስ አበባ ሻምፒዮና ሆነናል፤ ታዲያ አሸናፊ ስንሆን ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር ነበር፡፡ አሰልጣኝ እስከሆንክ ድረስ በሙያህ እየቆየህ ስትሄድ እርካታው ብቻ በቂ አይሆንም፤ ውጤት ማምጣት ይጠበቅብሃል፡፡ ውጤታማ የአጨዋወት ዘዴ ስፈጥርም እኔን በሚያስደስተኝና በማምንበት መንገድ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ደግሞ ኳስ የሚችሉት ልጆች ቀጫጭኖቹ ናቸው፡፡ እኔ በምርጫዬ ባለ ተሰጥኦዎቹን አስቀድማለሁ፡፡ በምይዛቸው ቡድኖች ውስጥም ተጫዋቾቼ ጥሩ ጨዋታ እንዲያሳዩ እፈልጋለሁ፡፡ እግርኳስ የአዕምሮ፣ የተሰጥኦና የአካል ብቃት ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ አንድ ላይ ሲገናኙ ጥሩ ነገር ማሳየት ይቻላል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የእግርኳስ አዕምሮ ወሳኝ ነው፡፡ አስተሳሰብና ተሰጥኦ ሲጣመሩ ደግሞ ግሩም ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እድሉ ከእኔ በፊት በመብራት ኃይል <C> ቡድን ወድቋል፡፡ እርሱ ፒያሳ ማዘጋጃ ሜዳ ሲጫወት አይቼው “እኔ ጋር ና፡፡” አልኩት፡፡ ከዚያ ትልቅ ተጫዋች ሆነ፡፡
የመብራት ኃይል የ<C> ቡድን ቆይታህ ለምን በአጭር ተቋጨ? እንምትጠቅስልን አይነት ውጤታማ ወጣት ተጫዋቾችን የማፍራት ብቃትህ እዚያው ክለብ ውስጥ ቆይተህ በአሰልጣኝነት የማደግ ተስፋ አልሆነህም?
★ የእኔ ዋናው ችግር ተመሳስሎ የመኖር ልምዱ የሌለኝ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ብዙ ጎድቶኛል፡፡ በመብራት ኃይልም ሆነ በሌሎች ክለቦች የማምንበት አሰራር ከሌለ ተስማምቼ መቀጠል ይቸግረኛል፡፡ እኔ በስልጠና ህይወቴ ከሁለት ክለቦች በላይ ተባርሬ የማውቅ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ተጣልቼ የምለቃቸው ቡድኖች ይበዛሉ፡፡ በዚያን ወቅት የመብራት ኃይል ክበብ ኃላፊ የነበሩት ሰው (ሥማቸውን መጥቀስ አያሻም፡፡) በምግብ ሰዓት “አስራ ስምንቱ ብቻ ይመገቡ፡፡” ብለው ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ <Out-of- Bench> የሚሆኑት እኮ ህጻናት ናቸው፡፡ ምናለበት ከልምምድ መልስ ቢመገቡ? በተጫዋቾች ምርጫ ጉዳይ በክለቡ ጽ/ቤት ብቻ ቁጭ ብዬ እንድመዘግብ ስታዘዝም አልስማማም ነበር፡፡ ምክንያቱም ‘እኔ የመረጥኳቸውን ይዤ እመጣለሁ፤ ክለቡ ምዝገባውን ያካሂድ፡፡’ የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ አድገው ትልቅ ደረጃ የደረሱት በሙሉ ቀድሜ ሜዳ ሲጫወቱ አይቻቸዋለሁ፡፡ አሰልጣኝ እንዳለ ሳያውቁ የሚጫወቱና አሰልጣኝ መኖሩን ተረድተው ለምርጫ የሚጫወቱት እኩል ብቃት የላቸውም፡፡ የፕሮጀክት ሥልጠና ላይ የሚስተዋለው ችግር እኮ ይኸው ነው፡፡ ወላጅ ከፍሎለት ለሥልጠና የሚመጣና በየሜዳው ሲጫወቱ መልምለህ የምታመጣቸው ልዩነት አላቸው፡፡ ተሰጥኦ የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በእነዚህና ሌሎች ትንንሽ ጉዳዮች እንጨቃጨቃለን፡፡ በክለቡ ሶስት ዓመት ቆይቻለሁ፤ ጥሩ ሥራ ሰርቻለሁ፤ በርካታ ተጫዋቾችን አፍርቻለሁ፤ ከፍተኛ የራስ መተማመን አዳብሬያለሁ፤… ስለዚህ ለቀቅሁና አየር መንገድ ገባሁ፡፡ በእግርኳሱ የማልደብቀው ነገር በአንዳንድ ቦታ ተመሳስለህ የመኖር ግዴታ ይጣልብሃል፡፡ በእርግጥ በፕሪምየር ሊጉ ራሳቸውን የሚያስከብሩ አሰልጣኞች አሉ፤ በእነርሱ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እነ ዮሃንስ ሳህሌ፣ ገብረመድህን ኃይሌና ሌሎችም ቀጥተኛ መሆናቸው ይጠቅማቸዋል፡፡ በተለይ በተለያዩ ክለቦች የሚሰሩ የኮሚቴ ኃላፊዎች <Professional> አይደሉም፡፡ ክለቦቹም የግል ስላይደሉ በሥራህ ብቻ የመመዘን ዕድልህ ጠባብ ይሆናል፡፡ በመንግስት ክለቦች እኮ ” ይጋጫል፤ ባህርዩ አስቸጋሪ ነው፤…” ብዙ ትባላለህ፡፡ ካልተመሳሰልክ፣ ካንዱ ጋር ከተጣላህ፣ በሆነ አቋምህ ካልተስማማህ፣…ቂም ይያዝብሃል፤ ከዚያ አንተ ሳታውቅ በአንተው ጉዳይ ስብሰባ ተቀምጠው ይፋለሙብሃል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች እንዳትሰራ ማነቆ ይሆኑብሃል፡፡ የምዋሸው ነገር አይደለም፥ እኔም ጋር ድክመት አለ፡፡ ስሜታዊ እሆናለሁ፤ አንዳንዴ የክለቦችን መመሪያ በአግባቡ አላከብርም፤ በተለይ ውጤት ሳገኝ የማደርጋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን በሒደት እነዚያን አሉታዊ ባህርይዎቼን እያስተካከልኩ ነው፡፡ ማጎብደድ ሳይሆን የምጠየቀውን ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በሥርዓት አቀርባለሁ፡፡ የተጎዳሁበትም ጉዳይ ስለሆነ ይህን ስህተቴን አርማለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደ ስራዬ አላደግኩምና፡፡
ይህ ባህርይህ እየጎዳህ እንደሆነ አሁን ገና ነው ያወቅኸው? የምታሰለጥናቸው ክለቦች ደረጃ እየወረደ መሄዱን ስታይ ችግርህን ማስተዋል አልቻልክም?
★ አዎ! ችግሮቼን መረዳት የጀመርኩት በቅርብ ነው፡፡ በፕሪምየር ሊጉ የሁለቱ ክለቦች (መድን እና አየር ኃይል) መውረድ ነገሮችን አበላሽቶብኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ዕምነት ታጥቶብኛል፡፡ “የቀድሞ ስሜን ለመመለስ ከታች ጠንክሬ ሰርቼ ቡድን ማሳደግ አለብኝ፡፡” የሚል ቁጭት አደረብኝ፡፡ ከዚያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባሳደኩት ቡድን ቆይቼ ችሎታዬን ማሳየት የሁልጊዜ እቅዴ ሆነ፡፡ ለምሳሌ በሰበታ ብቆይ “የምሰራውን አውቃለሁ፤ ከዚያ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡” የሚል ዕምነት አሳድሬያለሁ፡፡ በእርግጥ የግል ችግሮች የታየብኝ ጅማ ሳለሁ ስሜታዊ በመሆኔ ይመስለኛል፡፡ ከጅማ ከወጣሁ በኋላ ግን በደንብ አስቤበት አካሄዴን መቀየር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ በእግርኳስ ዋንጫ አስገኝተህም ትባረራለህ፥ ክሬዲት አይያዝልህም፡፡ ስለዚህ ‘ለምን ከሰዎች ጋር እጋጫለሁ?’ በሚል በሰበታ ምንም ግጭት ውስጥ ሳልገባ ጥሩ ቡድን ሰራሁ፡፡ ከአመራሮቹ ጋርም ተግባብቼ ቆየሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ሙያተኛ ያልሆነ ሰው ስለሚጠይቀን ሪፖርት ማቅረብ የማልወደው ሥራ ነበር፡፡ እሱንም አስተካክዬ ማቅረብ ጀመርኩ፡፡ ዘንድሮ ከራሴ ብዙ ነገር ጠብቄ ስለነበር የሰበታ ሥራዬን ሳጣ በጣም ተበሳጭቻለሁ፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ የሰበታ ቆይታዬ አልተራዘመም፡፡
“በየሰፈሩ የሚካሄዱ ደማቅ የእግርኳስ ውድድሮች ላይ ክፍሌ ቦልተና አይጠፋም፡፡” ይባላል፡፡ የእንደዚህ አይነቱ ውድድሮች ቀበኛ የሆንከው ለምልመላ ይሆን?
★ እኔ በምንም የስልጠና ማዕቀፍ ያልተያዙ ታዳጊዎች ኳስ ሲጫወቱ ማየት ደስ ይለኛል፡፡ ከድሮ ጀምሮ ህጻናት እስከ አስራ ሶስት ዓመታቸው ድረስ ባይሰለጥኑ ብዬ እከራከር ነበር፡፡ በሥልጠና ተጫዋቹን ” የራስህን ተውና የእኔን ተከተል፡፡” ብዬ በአዕምሮዬ ብቻ ያለውን እንዲለማመድ ላስገድደው እችላለሁ፡፡ ህጻናቱ የራሳቸውን ክህሎት ይዘው ካደጉ በኋላ በስልጠናው ችሎታቸውን ጠብቀህ ወደ ቡድን ሥራ ታስገባቸዋለህ፡፡ ይህን ለመረዳት በራሳቸው ሲጫወቱ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ እኔ ጅማም የሰፈር ጨዋታዎች አያለሁ፡፡ ተጫዋቾቹ በነጻነት በሜዳ ላይ ሲጫወቱ ተዓምር ነው የማየው፡፡ ሙያተኛ ለእነዚህ ልጆች የሚጎድላቸውን ብቻ ቢሰጣቸው፣ ችሎታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የአካል ብቃታቸውን፣ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናቸውን በማሳደግ የቡድን ሥራዎች ውስጥ የሚከታቸው አሰልጣኝ ቢያገኙ ጥሩ ይሆናል፡፡ ካልሆነ አንድ አሰልጣኝ ሙሉ በሙሉ ተሰጥኦ አያመጣም፡፡ መልምለህ አምጥተህ እኮ መጨረሻ ላይ አንድም ተጫዋች ላታወጣ ትችላለህ፥ እግርኳስ የተሰጥኦ ጉዳይ ነዋ፡፡ መጀመሪያ ይህን ማመን አለብን፡፡ በተለይ ክለብ ያልሰለጠኑት በሰፈር በሰፈር ተቧድነው ሲጫወቱ በርካታ ልጆችን እናገኝ ነበር፡፡ አሁን እንዲያውም ሜዳ ስለጠፋ ይህን ንጹህ እግርኳስ የምታይበት ሁኔታ የለም፡፡አሁንም ቢሆን በብሄራዊ ሊጉና ከፍተኛ ሊጉ የወዳጅነት ግጥሚያዎችን አያለሁ፡፡ አዘወትሬ መድን ሜዳና ኦሜድላ ሜዳ ማንም ሳያየኝ ከሩቅ ሆኜ እከታተላለሁ፡፡ ማናችንንም የሚያስደስት እግርኳስ የሚካሄደው በእንደነዚህ ያሉ ቦታዎች እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ተጫዋቾችን ለመለየትም ለእርካታም ደማቅ ውድድሮች ላይ እታደማለሁ፡፡
ከ1980ዎቹ አጋማሽ እስከ ሚሊኒየሙ ዋዜማ ድረስ መብራት ኃይል በርካታ ባለተሰጥኦ ወጣት ተጫዋቾችን ያወጣ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሒደቱ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፤ ጭራሽ የተጫዋቾቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አንተ ከዚያ ቀደም በዚሁ ክለብ የወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት ሥራ ትሰራ ስለነበር የችግሩ መነሻ ምንድን ይመስልሃል?
★ ችግሩ ፈረንጆቹ አሰልጣኞች መቀጠር ከጀመሩ በኋላ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክለቡ የውጪ ተጫዋቾች ማስመጣት ተጀመረ፡፡ ስለዚህ እድገቱ ቆመ፡፡ ኤልያስ ጁሃር ወደ ውጪ ከሄደ በኋላ ደግሞ ተጫዋቾችን የማሳደግ ልማዱ መቀዛቀዝ ያሳየበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የጣልያኖቹ ድርጅት ሳሊኒ ነበር የአሰልጣኞቹን ደመወዝ የሚከፍለው፡፡ የውጪዎቹ አሰልጣኞች የክለቡን ባህል ለማስቀጠል ከመጣር ይልቅ ውጤት ማምጣቱ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ነገርግን ውጤቱም አልተሳካም፤ የክለቡ ተጫዋቾች የማሳደግ ፖሊሲም አልቀጠለም፡፡ ጭራሽ በመብራት ኃይል ታሪክ ባልተለመደ መልኩ ከሌሎች ክለቦች በላቀ የተጫዋቾች ግዢ ላይ መሰማራት አዲስ አሰራር ሆነ፡፡ እንግዲህ ቡድኑ ወደ ከፍተኛው ሊግ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ በብዛት የውጪ ተጫዋቾችን ይይዝ ነበር፡፡ ነገርግን ከአምና ጀምሮ የቀድሞውን ባህል ለመመለስ ትግል ላይ ናቸው፡፡ የአሁኑ የክለቡ ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳያስን በቅርበት ባላውቀውም ብዙዎች ቀና ሰው እንደሆነና ቡድኑ ወደ ቀድሞ ዝናው እንዲመለስ የማያደርገው ነገር እንደሌለ ያወሩለታል፡፡ ድሮ ለክለቡ የተጫወቱትን ሰዎች አሰባስቦ ጥንድ ጥንድ በመሆን በእየርከኑ ቡድኖችን ይዘው እንዲሰሩ እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ በፈረንጆቹ መምጣት የወጣቶች ፖሊሲው እንደተቋረጠ አስባለሁ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ በክፍያም ሆነ በተጫዋቾች አያያዝ ከማንም ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ቡድን ነበር ኤልፓ፡፡ ግን ወደ ታች ወረደ፤ ይሄ ደግሞ ከባህሉ የማፈንገጡ ውጤት ይመስለኛል፡፡ አምና በሰበታ ሳለሁ በአንድ ምድብ ነበርን፡፡ ወጣቶችን ከእነ ታፈሰ ተስፋዬ ጋር በማዋሃድ ኤልፓን ወደ ላይ ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ ላስተውል ችያለሁ፡፡ ክለቡ የአሁኑን አይነት መሪ ከበፊት ጀምሮ ቢይዝ ኖሮ አሁን ያለበት ደረጃ አይደርስም ነበር፡፡
በቅርብ ከነበርክና የምታውቀው ነገር ካለ የውጪዎቹ አሰልጣኞች ወጣቶችን የማሳደግሒደቱን አይፈልጉም ነበር? ወይስ “አያዋጣንም!” ብለው ይሆን?
★ መጀመሪያ ወጣቶቹን ወርደው የሚያዩ አይመስለኝም፡፡ ማንም ሰው’ኮ የተጫዋቾቹን አቅም ሳያይ ውጤት የሚያስገኙ አይመስለውም፡፡ እንግዲህ በጊዜው ሲመረጡ የነበሩ ተጫዋቾች ከውጪ የመጡትም ሆነ ከሌሎች የሃገሪቱ ክለቦች የተዘዋወሩት ግዙፍ ተክለሰውነትና ከፍተኛ የአካል ብቃት ያላቸው እንደሆኑ እናስታውሳለን፡፡ በፊት መብራት ኃይል የሚታወቅበት እንቅስቃሴም ጠፍቶ ሰንብቷል፡፡ የውጪዎቹ አሰልጣኞች ያላዩአቸው ተጫዋቾች ከ<B እንደሆኑ> ሲረዱ እምነታቸው ይሸረሸራል፡፡ ከክለብ ክለብ እንዲሁም ከሃገር ሃገር እየተዘዋወሩ የሚጫወቱት ላይ ጥሩ አመኔታ ይጥላሉ፡፡ ስለዚህ ባህሉ እንዴት ይቀጥል? ከአምና ጀምሮ ግን ያላዋጣው ፖሊሲ ቆሟል፡፡ ቡናም ተመሳሳይ አቋም ወስዷል፡፡ መከላከያ ደግሞ ከሁሉ ይቀድማል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱትም ያን ፖሊሲ በአግባቡና በጥልቀት ገምግመው ይመስለኛል፡፡
የአየር መንገድ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር?
★ ከኤልፓ <C> ስለቅ አየር መንገድ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር፡፡ ክለቡ አሰልጣኝ የፈለገው ለ<B> ቡድኑ ነበር፡፡ ሄጄ ሳመለክት በመብራት ኃይል የሰራሁትን ስለሚያውቁ ወዲያው ተቀበሉኝ፡፡ እኔም <B> ቡድኑን ያዝኩ፡፡ የአየር መንገድ ዋናው ቡድን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ነበር፡፡ አስራት በብሄራዊ ቡድን የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮን ሆኖ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ክለቡን ሲለቅ እኔ በማሰለጥነው ወጣት ቡድን ውስጥ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ስለነበሩ ዋናውን ቡድን እንድይዝ ተደረግሁ፡፡ ከዚያ ዋናውን ቡድን ማሰልጠን እንደጀመርኩ ከ<B> ቡድኑ ወደ አስራ አራት ልጆች ወደ ላይ አሳደግሁ፡፡ አንድ ዓመት ከሰራሁ በኋላ የአየርመንገድ ሥራ አስፈጻሚ “ድርጅቱን ለማስተዋወቅ የእግርኳስ ቡድኑ ያን ያህል አያስፈልግም፤ አየርመንገድ ለስፖርቱ አላስፈላጊ ወጪ እያወጣ ነው፡፡” በሚል ሐሳብ ቡድኑ ለመፍረስ በቃ፡፡
ይቀጥላል…
©ሶከር ኢትዮጵያ