የ2012 ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጦች (ኅዳር 21 – ታኅሳስ 20)

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን ከተጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል። በአንድ ወር ውስጥ የ5 ሳምንታት 40 ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን በነዚህ ጨዋታዎች በተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች መሠረት የተጫዋቾች ደረጃ እና የወሩ ኮከቦችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

* ሊጉ ኅዳር 21 የተጀመረ ሲሆን ታኅሳስ 20 አንደኛ ወሩን አስቆጥሯል።

የወሩ ኮከብ ተጫዋች

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ፋሲል ከነማን ለቆ ወደ ባህር ዳር ከተማ ያመራው ፍፁም በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የተገነባው አዲሱ ባህር ዳር ከተማ የልብ ትርታ ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም። ከተጀመረ 5ኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በማጥቃቱ ረገድ ከዐምናው በእጅጉ ተሻሽሎ ለቀረበው ባህር ዳር ከተማ የፍፁም ዝውውር ዐምና የግብ እድሎችን ለመፍጠር ለሚቸገረው ቡድኑ ፍቱን መፍትሔ የሰጠ ስለመሆነ መናገር ይቻላል። ተጫዋቹ እስካሁን ድረስ በግሉ የግብ እድሎችን ከመፍጠር በዘለለ የማጥቃት እንቅስቃሴን በመምራት ረገድ ቡድኑ በሊጉ ጥሩ የውድድር ዓመት ጅማሮን በማድረግ ላይ እንዲገኝ አስችሏል።

5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር በውድድር አመቱ በ5 ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው 9 ጎሎች ውስጥ ገሚሱ በፍጹም የተቆጠሩ ሲሆን በተለይ ቡድኑ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም መቐለ 70 እንደርታን 3-2 ሲረታ ሦስተኛ ግብ ላይ ሦስስ የመቐለ ተከላካዮችና ግብጠባቂውን አታሎ ያስቆጠራት ግብ ተጫዋቹ የሚገኝበትን ከፍ ያለ የራስ መተማመን ያሳየች አስደናቂ ግብ ነበረች።

የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ – ዮሐንስ ሳህሌ (ወልዋሎ)

ወልዋሎን ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ የተረከቡት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ለደርዘን የቀረቡ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ይዘው ከመሄዳቸው አንፃር ቡድኑ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት በውህደት ደረጃ ሊቸገር ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም ግምቶችን ባፋለሰ መልኩ ቡድኑ አስደናቂ አጀማመርን ማድረግ ችሏል። እስካሁን ካደረጓቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥ 3 አሸንፈው፣ 1 አቻ ተለያይተው እንዲሁም በ1 ጨዋታ ተሸንፈው በ10 ነጥብ ሊጉን ከመቐለ ጋር በጣምራ መምራት ላይ ይገኛሉ።

በመከላከል አደረጃጀቱ የተዋጣለት ቡድን በመገንባት የተካኑት አሰልጣኙ ዘንድሮም ተመሳሳይ ቡድን በወልዋሎ እያሳዩን ይገኛሉ። በተጨማሪም ቡድን በመልሶ ማጥቃት እጅግ ፈጣን የሆኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን በመያዙ ለቡድኖች አይምሬ ስለመሆቸው እያስመሰከሩ ይገኛል።

ከዚህ ጠንካራ ጅማሮ ጀርባ የሚገኙት አሰልጣኙ ከግብ ጠባቂያቸው አብዱልአዚዝ ኬይታ ውጭ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተዋቀረው የቡድኑ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች በፍጥነት ተዋህደው ውጤት እንዲያስመዘግብ ከማስቻል በዘለለ የቡድን ስብስባቸውን በተለዋዋጭ ሚና በመጠቀምና በሌሎች ክለቦች እምብዛም የመሰለፍ እድል ባላገኙ ተጫዋቾች ይህን ውጤት ለማስመዝገብ መብቃታቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ተግባርን መከወን ችለዋል።

የወሩ ምርጦች በቁጥራዊ መረጃዎች

ጎል + ለግብ የሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት

የሊጉ ክብራቸውን የማስጠበቅ ጉዟቸውን በሂደት ወደ ትክክለኛው መስመር እየመለሱ ለመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከዚህ መሻሻል ጀርባ እንደ ዐምናው ሁሉ የአማኑኤል ድርሻ የጎላ ነው። በሁሉም የሊግ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት መሰለፍ የቻለው አማኑኤል ጎልቶ የወጣ እንቅስቃሴ ሳያደርግ በወጣባቸው ጨዋታዎች ጭምር በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ በሚያደርገው አበርክቶ አሁንም ልዩነት መፍጠሩን ቀጥሏል። እስካሁን በሊጉ አራት ግቦችን በማስቆጠርና ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ይህን ሰንጠረዥ ከአናት ሆኖ ይመራል።

ምስል፡- በበርካታ ጎሎች ላይ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተጫዋችች (ጎል + አሲስት)

ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል

የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ ሐብታሙ ገዛኸኝ እስካሁን ድረስ አራት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በሊጉ ከሚገኙ ተጫዋቾች ቀዳሚው መሆን ችሏል። በፈጣን ሽግግሮች የግብ እድሎችን ሲፈጥር በሚስተዋለው ቡድን ውስጥ የሚገኘው አጥቂው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች ጀርባ ወደ መስመር አድልተው የሚገኙ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ እንዲጠቀሙ አመቻችቶ በማቀበል ጥሩ የውድድር ጅማሮን እያደረገ ይገኛል።

ምስል፡- በወሩ በርካታ ኳሶችን ለጎል ያመቻቹ ተጫዋቾች

ግብን ያለማስደፈር

በ5 ሳምንት የሊጉ ቆይታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብጠባቂ ባህሩ ነጋሽ እስካሳለፍነው ሳምንት ድረስ ግቡን ሳያስደፍር በመቆየት ይመራል። በጠንካራ የተከላካይ መስመር ከመታጀቡ በመነጨ በቂ የግብ ሙከራዎች ሲደረጉበት የማይስተዋለው ባህሩ በግሉ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። ከእሱ ቀጥለውም የአዳማው ጃኮ ፔንዜና የጅማው ሰዒድ ሀብታሙ በሶሶት ጨዋታዎች መረባቸውን ያላስደፈሩ ግብጠባቂዎች ናቸው።

ምስል፡- በወሩ በበርካታ ጨዋታዎች መረባቸውን ያላስደፈሩ ግብ ጠባቂዎች

ጎል ለማስቆጠር አማካይ ደቂቃ

የሊጉን የከፍተኛ ጎል ደረጃን ሙጂብ ቃሲም ይመራዋል። በጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ የሚገኙ ተጫዋቾች ከተጫወቱበት ደቂቃ አንፃር በመመዘን በተሰራው ደረጃም የፋሲል ከነማው አጥቂ በቀዳሚነት ቀምጧል። የሀዋሳ ከተማው ወጣት አጥቂ ብሩክ በየነም ሁለት ጊዜያት ተቀይሮ በመግባት በንፅፅር ዝቅተኛ ደቂቃዎች በመጫወት አራት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

ምስል፡- ተጫዋቾች አንድ ጎል ለማስቆጠር የሚፈጅባቸው አማካይ ደቂቃ


© ሶከር ኢትዮጵያ