ወልቂጤ ከተማ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታውን በሜዳው ያከናውናል

በፕሪምየር ሊጉ አብይ ኮሚቴ ዕድሳት ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከነበሩት ሜዳዎች መካከል አንዱ የነበረው የወልቂጤ ስታዲየም ዕድሳቱን በማጠናቀቁ የፊታችን ቅዳሜ ወልቂጤ በሜዳው ስሑል ሽረን ለመጀመሪያ ጊዜ ይገጥማል፡፡

ወደ ፕሪምየር ሊጉ አዲስ ካደጉት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ወልቂጤ ከተማ በሜዳው ማድረግ የነበበትን ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ለማድረግ ተገዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሜዳው ለፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ሲባል መሻሻል አለበት በሚል በዐቢይ ኮሚቴው ውሳኔ በመተላለፉ የሜዳው ላይ ጨዋታዎቹን በባቱ ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ እና እንዲሁም በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሲያደርግ ቆይቷል።

ዕድሳት ሲደረግለት የነበረው የወልቂጤ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳውን በሳር ንጣፍ ከማልበስ አንስቶ የአጥር ሥራዎችንም ጭምር ያለፉትን ጊዜያት ሲከናወንበት ከቆየ በኃላ የፕሪምየር ሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ ተመልክቶት ብቁ ነው በማለቱ በስድስተኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው በመግጠም ሀ ብሎ ይጀምራል፡፡ አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ቡድኑ ለሊጉ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ወደ ሜዳቸወረ መመለሳቸው ዕፎይታን እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡

በሊጉ እስከ አሁን ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ምንም የግብ ዕዳ ሳይኖርበት በሰባት ነጥቦች ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ