ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ በሰበታ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መካከል በሚደረገው ጨዋታ ይጀምራል። ጨዋታውንም በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

የውበቱ አባተ ቡድን ድብልቅ የጨዋታ ዘይቤን (ቀጥተኛ እና ኳስ ይዞ መጫወት) የሚከተል ይመስላል። በተለይ ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ጨዋታውን ሲያከናውን እንደ ተጋጣሚው ክፍተት አጨዋወቱን ሲቀያይር እና ውጤት ለማግኘት ሲጥር ታይቷል። ለእዚህ ሁለት አይነት አጨዋወቶች የሚሆኑ ተጫዋቾችን ቡድኑ በመያዙ በቀጣይም ሊጠቀም ይችላል። ይህም ጉዳይ በዛሬውም ጨዋታ ቡድኑ እንዳይገመት ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይታሰባል። ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ተጨዋቾች የተለያዩ የጎንዮሽ እና ቀጥተኛ ሩጫዎችን በማድረግ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ለመረበሽ ስለሚጥሩ ለወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ጎል ያስቆጠሩት ፍፁም እና አስቻለው በሁለተኛ የግቡ ቋሚ (far post) በመገኘት ጎሎችን ለማነፍነፍ ስለሚሞክሩ ለቡድናቸው በጎ ነገር ለማስመዝገብ ጥሩ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ ላይ የታየው ያልተደራጀ የተከላካይ መስመር መፍትሄዎችን በቶሎ ካላገኘ ነገ ሊፈተን ይችላል። በተለይ ቡድኑ የትኩረት ማነስ ችግር እና የሰንጣቂ ኳሶችን የሚከላከልበት መንገድ መሻሻሎችን ይሻሉ።

ረጅም ጉዳት ላይ የሚገኘው አንተነህ ተስፋዬን ጨምሮ ሳቪዮ ካቩጎ እና ባኑ በጉዳት ለጨዋታው አይደርሱም።

ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስር ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ማጥቃትን ተቀዳሚ ምርጫው አድርጎ እንደሚገባ ይታወቃል። ይህ የቡድኑ ባህርይም በዛሬው ጨዋታ መጠነኛ የጥንቃቄ አቀራረብ ታክሎበት እንደሚታይ ይጠበቃል። ቡድኑ በመጀመርያው ሳምንት ሲዳማ ቡናን ካሸነፈ በኋላ ከድል በመራቁም ከዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘትን አላማ አድርጎ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ቡድኑ ከተከላካይ አማካይ ፊት በሚገኙ በአራት አማካዮቹ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት ተጠቅሞ ለማጥቃት የሚሞክረውን የሰበታ እንቅስቃሴን ለመግታት ቀለልፍ መሳርያ እንደሚሆን ይገመታል። በተጨማሪም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የባዬ ገዛኸኝ እና የመስመር አማካዩ ቸርነት ጉግሳን ፍጥነት በመጠቀም አደጋ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው። በተለይም ጎሎች እያስተናገደ የሚገኘውና የተሟላ የውህደት ደረጃ ላይ ለመገኘት የተቸገረው የሰበታ የኋላ መስመርን በምን መልኩ ይጠቀምበታል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

ወላይታ ድቻ በረከት ወልዴን ረዘም ካለ ጉዳት መልስ ሲያገኝ ያሬድ ዳዊት እና ነጋሽ ታደሰ ግን በጉዳት አሁንም አገልግሎት አይሰጡም።

እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የመጀመርያ ግንኙነታቸው ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃ/ማርያም – ወንድይፍራው ጌታሁን – አዲስ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

ደሳለኝ ደባሽ – መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ

በኃይሉ አሰፋ – ፍፁም ገ/ማርያም – አስቻለው ግርማ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መኳንንት አሸናፊ

ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – ይግረማቸው ተስፋዬ

ተስፋዬ አለባቸው

ዘላለም እያሱ – እንድሪስ ሰዒድ – እዮብ አለማየሁ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ