ሦስት የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ከፋሲል ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ከቡድኑ ጋር አልተጓዙም

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በጣና ሞገዶቹን ቤት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ሦስት ተጫዋቾች ልምምድ አቁመዋል። ቅዳሜ ለሚደረገው ጨዋታም ከቡድኑ ጋር ወደ ጎንደር አልተጓዙም።

ከቡድን አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ልምምድ ያላከናወኑት ተጨዋቾች አዳማ ሲሶኮ፣ ሃሪስተን ሄሱ እና ማማዱ ሲዲቤ ናቸው። ተጨዋቾቹ ቡድናቸው ወደ ሆሳዕና አምርቶ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ መልስ በተደረጉ አራት የልምምድ መርሃ ግብሮች ላይ እንዳልተሳተፉ ታውቋል። በተጨዋቾቹ በኩል በተሰማ ዜና ልምምድ ያቆሙት ከደሞዝ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ተነግሯል።

የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ወደ ጎንደር አምርተው ነገ ፋሲል ከነማን የሚገጥሙት የጣናው ሞገዶቹ ትላንት ጎንደር ከተማ ገብተዋል። ሶስቱ ተጨዋቾችም መደበኛ ልምምዶችን ስላላከናወኑ እና ወደ ጎንደር ለመጎዝ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከስብስቡ ውጪ እንደሆኑ ታውቋል።

ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን የክለቡን ስራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ጥያቄ አቅርበንላቸው አጭር ምላሽ ሰተውናል።” መረጃው ትክክል ነው። ሦስቱም ተጨዋቾች ልምምድ አቁመዋል። አሰልጣኙም መደበኛ ልምምድ ስላልሰሩ ወደ ጎንደር ይዟቸው አልተጓዘም። በእኛ በኩል ግን ንግግሮችን እያደረግን ነው። በቀጣይ ጨዋታ ይህ ጉዳይ እንዲፈታ እንጥራለን።”

ሦስቱ ተጨዋቾች ከዚህ ቀደም ቡድናቸው ጅማ አባጅፋርን ሊገጥም ወደ አዳማ ሲጓዝ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ከስብስቡ ተለይተው ወደ ስፍራው እንዳመሩ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ