ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ማንሰራራቱን ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ሰበታ ከተማ በፍፁም ገ/ማርያም ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1-0 አሸንፎ ከመጥፎ የሊጉ አጀማመሩ ማንሰራራቱን ቀጥሏል።

ሰበታ ከተማዎች በሳምንቱ መጨረሻ በተጨማሪ ደቂቃ በተገኙ ሁለት ግቦች ከጠንካራው ፋሲል ነጥብ ከተጋራው ቡድን ውስጥ የሦስት ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ወንድይፍራው ጌታሁን፣ ታደለ መንገሻ እና ኢብራሂም ከድር ወደ በመጀመሪያ ተመራጭነት ተካተዋል። በወላይታ ድቻዎች በኩልም እንዲሁ በወልቂጤ ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ሁለት ቅያሬዎችን አድርገዋል፤ በዚህም እዮብ ዓለማየሁ እና ዘላለም ኢያሱን አስወጥተው በምትካቸው ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው በረከት ወልዴ እና ዳንኤል ዳዊትን በማስገባት ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመስመር አጥቂነት የተሰለፉት ተጫዋቾች በጥልቀት ወደ መሐል ተስበው መጫወታቸው ይበልጥ መሀል ሜዳው በተጫዋቾች እንዲጨናነቅና ይህ ነው የሚባል የረባ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዳንመለከት አይነተኛ አስተዋጽኦ ነበረው። የጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ የተገኘችው በ12ኛው ደቂቃ ነበር፤ የሰበታው አሊ ባድራ ከቀኝ መስመር አጥብቦ ወደ ውስጥ ገብቶ ከድቻ የሳጥን ጠርዝ የሞከረውን ኳስ መኳንንት አሸናፊ ሊያድንበት ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ተደራጅቶ በመከላከል የመልሶ ማጥቃት የመጫወት እቅድ እንዳላቸው በግልፅ መታየት የጀመሩት ድቻዎች በ20ኛው እና 35ኛው ደቂቃ የሰበታ ተጫዋቾች በሰሯቸው የቅብብል ስህተቶች የተገኙትን ሁለት አጋጣሚዎች በአደገኛ ቀጠና ውስጥ ቢያገኙም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በተለይም በ20ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከበረኛው በጥቂት ርቀት አግኝቶ ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች።

በሒደት ኳስን በመቆጣጠር ወደፊት በመሄድ ረገድ መሻሻልን ያሳዩት ሰበታዎች በ21ኛው በ30 እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ በፍፁም ገ/ማርያም እንዲሁም በሁለቱ አጋጣሚዎች አስቻለው በቀጥታ የሞከሯቸው ሙከራዎች አደገኛ የነበሩ ሲሆን በሁለቱ አጋጣሚዎች መኳንንት በግሩም ብቃት ሊያድንባቸው ችሏል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም (38ኛው ደቂቃ) አስቻለው ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ሲመለስ የቡድን አጋሩ ኢብራሂም ከድር ያገኘውን እድል ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ በወላይታ ድቻው የመሀል ተከላካይ አንተነህ ጉግሳ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ገ/ማርያም በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህችም ግብ ለፍፁም በሁለት ጨዋታ ያስቆጠራት ሦስተኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች።

ከግቧ መልስ ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ሰበታዎች በ40ኛው ደቂቃ ዓሊ ባድራ እንዲሁም ከግራ መስመር አንድ ተጫዋች አልፎ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ለጥቂት ወደደ ውጭ የወጣበት ኳስ የቡድኑን መሪነት ለማስፋት የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ዳዊት እስጢፋኖስን በኢብራሂም ከድር ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ሰበታዎች በተመሳሳይ ሁለተኛ አጋማሽ በተጀመረ በደቂቃዎች ልዩነት ጉዳት ያስተናገደው አስቻለው ግርማን በበኃይሉ አሰፋ ለመቀየር ተገደዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያስመለከተ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎች በሁለቱም በኩል ተፈጥረዋል። በ50ኛው ደቂቃ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ከጠበበ አንግል ወደ ግብ የላካት እንዲሁም 60ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ከረጅም ርቀት በቀጥታ የመታቸውን ኳሷች መኳንንት አሸናፊ ሊያድናቸው ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ የራስ መተማመን ለመጫወት የሞከሩት ድቻዎች በ68ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል አልፈው የሄዱትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ የሰበታ ተከላካዮች ተረባርበው ያዳኑበት እንዲሁም 70ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሸማውን ኳስ ደጉ ደበበ አመቻችቶ አቀብሎት ዳንኤል ዳዊት በማይታመን ሁኔታ ያመከነው ኳስ ድቻዎች ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘት ሊችሉባቸው የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በተቃራኒው በ74ኛው ደቂቃ ከመስመር ኃይለሚካኤል ያቀበለውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ታደለ መንገሻ አግኝቶ ከግብ በላይ የሰደዳት ኳስ ለሰበታዎች በተመሳሳይ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

ጨዋታው በሰበታ ከተማዎች የ1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማዎች ጥሩ ካልሆነ አጀማመራቸው ማግስት በመጨረሻ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች 7 ነጥቦችን በማሳካት በጊዜያዊነት ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ብለው ማንሰራራታቸውን ሲቀጥሉ ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደው ወደ 13ኛ ደረጃ ዝቅ ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ