የስድስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ ግብር የሆነው የሰበታ ከተማ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች በዚህ መልኩ ሰጥተዋል።
“ከማሸነፋችን በላይ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሄድንበት መንገድ ጥሩ ነበር” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)
ጨዋታው እንዴት ነበር?
ጨዋታው ለእኛ ጥሩ ጨዋታ ነበር። አንደኛ ማሸነፋችን፤ ሁለተኛ ደግሞ በጨዋታው ከበፊት ጨዋታዎቻችን ያሻሻልናቸው ነገሮች ስለነበሩ መልካም ነበር ማለት እንችላለን። የምንፈልገውን እንቅስቃሴ ለማሳየት እየሞከርን ነው። ከማሸነፋችን በላይ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሄድንበት መንገድ ጥሩ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበረው ደከም ያለ እንቅስቃሴ…?
ልክ ነው፤ በምንፈልገው አጨዋወት ውስጥ መዋዠቆች አያለሁ። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ኳስ ከኋላ መስርቶ ከመውጣት ይልቅ ረጃጅም ኳሶች ይለቀቁ ነበር። ስለዚህ ኳሶችን የራሳችን ማድረግ ስላልቻልን ተቸግረን ነበር። ይህ ደግሞ በቀጣይ በሂደት የሚሻሻል ነገር ስለሆነ ምንም ማለት አይደለም። በአጠቃላይ ግን ከሌሎች ጨዋታዎቻችን በተሻለ ለመንቀሳቀስ እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል።
አጨራረስ ላይ ቡድኑ ስላለበት ችግር…?
በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር መስራት ከባድ ነው። ከታች እጠግናለሁ ስትል ከላይ ያፈስብሃል። እኛ ደግሞ ትኩረት ሰተን የተነጋገርነው ከኋላ መስመር ያለውን ነገር ለማስተካከል ነው። በርካታ አጋጣሚዎችን ፈጥረን አምክነናል ማለት ወደ የሆነ ነገር እየገባን ነው ማለት ነው። ስለዚህ የፊት መስመራችንን እያስተካከልን እንቀጥላለን። ዋናው እኛ በምንፈልገው መንገድ ለመጫወት መሞከራችን ነው።
“እንደ ሁለተኛ አጋማሽ አጨዋወታችን በመጀመሪያው አጋማሽ ብንጫወት ኖሮ የተሻለ ነገር ይዘን እንወጣ ነበር” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ወላይታ ድቻ)
ጨዋታውን እንዴት አገኙት?
ጨዋታው ሁለት ገፅታ ነበረው። ከእረፍት በፊት ተጨዋቾቼ ይበልጥ ወደ ኋላ አፈግፍገው ነበር። ይህም ደግሞ ከተሰጣቸው ስራ ውጪ ነበር። ከእረፍት መልስ ደግሞ ይህንን ነገር አስተካክለን ለመቅረብ ሞክረናል። እንደ ሁለተኛ አጋማሽ አጨዋወታችን በመጀመሪያው አጋማሽ ብንጫወት ኖሮ የተሻለ ነገር ይዘን እንወጣ ነበር።
በራሳችሁ ድክመት ነው የተሸነፋችሁት ወይስ በተጋጣሚ ጥንካሬ?
እኔ ጥንካሬም ነው ድክመትም ነው አልለውም። ጎልም ያገቡብን በፍፁም ቅጣት ምት ነው። የፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ በዳኛው የሚወሰን ነው። እኛም እነሱ ካገኙት የፍፁም ቅጣት ምት የተሻለ የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ በእጅ በመነካቱ ልናገኝ ሲገባን አልተሰጠንም። በአጠቃላይ እነሱ ከእረፍት መልስ እኛ ሳጥን አካባቢ የደረሱት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ስለዚህ ያገኙትን እድል በአግባቡ ተጠቅመው ነው ያሸነፉን።
© ሶከር ኢትዮጵያ