ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ነገ በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የሚደረገውን የፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሜዳቸው የማይቀመሱ የሚመስሉት ፋሲል ከነማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሰበታ ያጡትን አስቆጪ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እና ደጋፊን ለመካስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚሰለጥነው ቡድኑ በተለይ ኳስን በትዕግስት በማንሸራሸር የተጋጣሚን ክፍተት ለማግኘት እንደሚጥር በተከታታይ ጨዋታዎች ታይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደየጨዋታ እንቅስቃሴው የአየር ላይ እና የመሬት ላይ ሰንጣቂ ኳሶችንም ፊት መስመር ላይ ላሉት ተጨዋቾች በመጣል ቡድኑ ግቦችን ሲያነፈንፍ ይስተዋላል። በነገውም ጨዋታ እንደ ባህር ዳር ከተማ የጨዋታ አቀራረብ ስልቱን በመቃኘት አጨዋወቱን ይለያል ተብሎ ይታሰባል።

የመሐል ተጨዋቹ ሱራፌል ዳኛቸው እና የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ የቡድኑ የልብ ምት ይመስላሉ። የቡድኑ የማጥቃት ሒደትም ከእነዚህ ታታሪ ተጨዋቾች እግር ሲወጣ እና ተጋጣሚን ሲፈትን ይስተዋላል። በነገውም ጨዋታ በጥሩ ብቃቱ ላይ ከሚገኘው እና የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ብቻውን ከሚመራው ሙጂብ ቃሲም ጎን ለጎን ሁለቱ ተጨዋቾች ወሳኝ ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት ከወገብ በታች (ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ) ያሉ ተጨዋቾች ያሳዩት የመዘናጋት እና የትኩረት ማነስ ስህተቶች በነገውም ጨዋታ ካልተቀረፈ ቡድኑን ሊጎዱ ይችላሉ።

በፋሲል በኩል እንየው ካሳሁን እና ያሬድ ባዬ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ ቀላል ልምምድ የጀመረው ሰለሞን ሀብቴ ወደ ቡድኑ ተካቷል።

ከጎንደር በ160 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት እንደ ፋሲል ሁሉ እየመራ (በሁለት አጋጣሚዎች) ነጥብ የጣለበትን ጨዋታ እያሰበ በቁጭት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ተጋጣሚው (ፋሲል ከነማ) ተመሳሳይ የጨዋታ ዘይቤን ለመከተል እንደሚሞክር የሚነገርለት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የነገው ጨዋታ ከሜዳው ውጪ እንደመሆኑ ጥንቃቄን ቅድሚያው ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል። ምንም እንኳን ቡድኑ ጥንቃቄን ቅድሚያው ያደርጋል ተብሎ ቢታሰብም በቡድኑ ውስጥ ያሉት ፈጣን እና አደገኛ ተጨዋቾች በጨዋታው ቡድኑን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚጥሩ ይጠበቃል። በተለይ በግራ እና በቀኝ መስመር ላይ እንደሚሰለፉ የሚጠበቀው ወሰኑ ዓሊ እና ግርማ ዲሳሳ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ፋሲል ከነማን እንደሚፈትኑ ይገመታል።

ከዚህ በተጨማሪ የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው ፍፁም ዓለሙ ከመሃል ሜዳ እየተነሳ የሚያደርጋቸው ሩጫዎች እና የኳስ ንክኪዎች አደገኞች ናቸው።

ከመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ (አዳማ ጋር ጅማን የገጠመበት) በስተቀር በአራቱ መርሃ ግብሮች ጎል እያሰተናገደ ያለው ቡድኑ ያለበትን የግብ ማስተናገድ አባዜ ካልቀረፈ ነገ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል።

በባህር ዳር በኩል ሦስቱ የውጪ ተጨዋቾች ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። በሦስቱ ዋና ዋና ክፍሎች የሚሰለፉት ሃሪስተን ሄሱ፣ አዳማ ሲሶኮ እና ማማዱ ሲዲቤ በነገው ጨዋታ አለመኖራቸው ቡድኑን እጅግ እንዲቸገር ያደርጋል። በተለይ ሲዲቤ እና ሲሶኮ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀማቸው እስካሁን ቡድኑን ሲጠቅም እንደመታየቱ ነገ በዚህ ረገድ ክፍተቶች እንደሚኖር እንዲጠበቅ ያደርጋል። በተለይም ባለፈው ሳምንት በሰበታ ሁለት የጭንቅላት ኳሶች የተቆጠረበት ፋሲል ከነማ ደካማ ጎንን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት እንደሚሆን ይገመታል።

ከሦስቱ ተጨዋቾች ውጪ ቡድኑ በቅጣትም ሆነ በጉዳት ተጨማሪ ተጨዋቾችን በነገው ጨዋታ እንደማያጣ ተሰምቷል።

9 ሰዓት የሚጀምረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ አማራጮች ጨዋታውን በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ዐምና ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያው ዙር ባህር ዳር ላይ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ 4-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ዓ/ብርሀን ይግዛው – ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኦሴይ ማዊሊ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

ሳላምላክ ተገኝ – ሰለሞን ወዴሳ – አቤል ውዱ – ሚኪያስ ግርማ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ፍፁም ዓለሙ

ወሰኑ ዓሊ – ስንታየሁ መንግስቱ – ግርማ ዲሳሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ