ወልቂጤ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው ጨዋታ የሚያደርግበትን መርሐ ግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በታሪክ የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በሜዳቸው የሚያካሂዱት ወልቂጤዎች ከወሳኝ የሜዳ ውጪ ድል በኋላ የድል ጉዟቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ባለፉት ጨዋታዎች ግዙፉ አጥቂ ጃኮ አረፋት ላይ ያነጣጠረ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ወልቂጤዎች በነገው ጨዋታ በርካታ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ቢያጡም ጨዋታው በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እንደመሆኑና ከአሸናፊነት እንደመምጣታቸው በጥሩ መነቃቃት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
እንደ ተጋጣሚያቸው አቀራረብ የሚቀያየር አጨዋወት ያላቸው ባለሜዳዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ሲያስፈልግ ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት በተቀሩት ደሞ ቀጥተኛ ኳስ የሚጠቀም ቡድን ያሳዩ ሲሆን በነገው ጨዋታ ግን የተጋጣሚያቸው ደካማ የመከላከል አቅም ለመጠቀም ረጃጅም ኳሶችን የሚጠቀሙበት እድል የሰፋ እንደሆነ ይገመታል።
ወልቂጤዎች በነገው ጨዋታ ሶሆሆ ሜንሳህ፣ ቶማስ ስምረቱ፣ በቃሉ ገነነ፣ አሳሪ አልመሐዲ፣ አሕመድ ሁሴን እና አዳነ በላይነህን በጉዳት አያሰልፉም።
ባሳለፍነው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ስሑል ሽረዎች ምንም እንኳ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ብዙ ባይባልም በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ እንደመጣላቸው ወደ ድል መመለስ ግድ ይላቸዋል።
በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በሚሞክሩ የመስመር አጥቂዎች የተዋቀረው ስሑል ሽረ ባለፉት የሜዳው ጨዋታዎች በተጠቀሰው አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ቢደርስም ዕድሎች ወደ ግብ የመቀየር ክፍተቶች ታይቶበታል።
በመጨረሻው ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታ በተለየ አቀራረብ ወደ ሳጥናቸው አፈግፍገው የጥንቃቄ ጨዋታ ለመጫወት የሞከሩት ሽረዎች ነገም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ እንደተከተሉት የጥንቃቄ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቡድኑ ከመስመር አጨዋወት ወጣ ያለ የማጥቃት አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ግን አይጠበቅም።
ሽረዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በተቃራኒው ዮናስ ግርማይ ቅጣቱን ጨርሶ የሚመለስ ተጫዋች ነው።
እርስ በርስ ግንኙነት
– የነገው ጨዋታ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙበት ነው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ይድነቃቸው ኪዳኔ
ይበልጣል ሽባባው – ዐወል አህመድ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዘር ኦቴ
ኤፍሬም ዘካሪያስ – በረከት ጥጋቡ – አብዱልከሪም ወርቁ
ሄኖክ አወቀ – ጃኮ አራፋት – ጫላ ተሺታ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ምንተስኖት አሎ
ዓብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ
አክሊሉ ዋለልኝ – ነፃነት ገብረመድህን
ዲድዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – ዓብዱልለጢፍ መሐመድ
ሳሊፍ ፎፋና
© ሶከር ኢትዮጵያ