ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሀዋሳ ከተማ

ቢጫ ለባሾቹ በሜዳቸው ሀይቆቹን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት የገጠማቸው የሊጉ መሪ ወልዋሎዎች ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል በመመለስ መሪነታቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር አድርገው የነበሩትና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦች የጣሉት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም በርካታ የተጫዋቾች ሚና እና የአሰላለፍ ለውጦች ይጠበቃሉ። ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተለመደው የመስመር እና ረጃጅም ኳስ አጨዋወቶች ስኬታማ ያልሆኑት ወልዋሎዎች በተጋጣሚ ሳጥን ላይ ያላቸው የቁጥር ማነስ ለማሻሻል ወደ ሁለት አጥቂዎች ጥምረት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከጅማ አባጅፋርና ከመቐለ ጋር ባደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ከግራ መስመር ከሳሙኤል ዮሐንስ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎች በተጠቀሱት ጨዋታዎች ለተጋጣሚ ቀላል የማጥቃት አጨወቶች ይዘው ቀርበዋል። በዚህም ይህን የግብ ዕድሎች ወደ ጎልነት የመቀየር ችግር ለመፍታት ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጁንያን ናንጂቡ በፊት ለፊት ያጣምራሉ ተብሎ ይገመታል።

ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ ዓይናለም ኃይለ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና አቼምፖንግ አሞስ በጉዳት፤ ግብ ጠባቂው ዓብዱልዓዚዝ ኬይታን ደግሞ በቅጣት አያሰልፉም።

እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ከጥሩ አጀማመር በኋላ ተከታታይ ጨዋታዎች በሰፊ ውጤት ተሸንፈው የተንሸራተቱት ሀዋሳዎች ከሁለቱም ጨዋታዎች የተለየ አጨዋወት ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከመጀመርያዎቹ ሳምንታት በተለየ አቀራረብ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያለው ቡድን ይዘው ቀርበው ውጤታማ መሆን ያልቻሉት እና በሁለቱ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገዱት ሀዋሳዎች በነገው ጨዋታ ወደ ቀደምት ጠጣር አቀራረባቸው የሚመለሱበት ዕድል የሰፋ ነው።

ሁለቱ ፈጣን አጥቂዎች መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ይገባሉ ተብለው ለሚጠበቁት ሀዋሳ ከተማዎች የማጥቃት አጨዋወት ይመራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

ሀይቆቹ በነገው ጨዋታ ቸርነት አወሽን በጉዳት አያሰልፉም። ከጉዳት የተመለሰው እስራኤል እሸቱም ወደ መቐለ አልተጓዘም።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች አራት ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ ሁለት ሲያሸንፍ፣ ሀዋሳ አንድ አሸንፎ በቀሪዋ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
– በአራቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎች ሲቆጠሩ ወልዋሎ 2፤ ሀዋሳ 3 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-4-2)

ጃፋር ደሊል

ምስጋናው ወልደዮሐንስ- ፍቃዱ ደነቀ- ገናናው ረጋሳ – ሄኖክ መርሹ

ሰመረ ሀፍታይ – ራምኬል ሎክ – ዘሪሁን ብርሀኑ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ኢታሙና ኬይሙኔ – ጁንያስ ናንጂቡ

ሀዋሳ ከተማ (4-4-2)

ቢሊንጌ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – መሳይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ ያኦ ኦሊቨር

ብርሀኑ በቀለ – አለልኝ አዘነ – ህኖክ ድልቢ – ዮሀንስ ሱጌቦ

ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ