ነገ በስድስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዲያ ሆሳዕና መርሐ ግብርን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
በእንቅስቃሴ ደረጃ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው የካሳዬ አራጌ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ተጉዞ ነጥብ ከጣለበት ጨዋታ መልስ የነገውን መርሃ ግብር ይጠባበቃል። በተለይ ቡድኑ በአራተኛ ሳምንት በሜዳው ሃዋሳን 4-1 ካሸነፈበት ጨዋታ በመነሳት ለውጦች እንዳሉበት ሲነገር ቢቆይም የሊጉን ደካማ ቡድን ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል።
በእንቅስቃሴ እና በውጤት ደረጃ እየተነቃቃ የመጣ የሚመስለው ቡድኑ በተለይ ተጋጣሚን የሚያደክሙ እና ክፍተት እንዲፈጥሩ የሚያስገድዱ የኳስ ቅብብሎችን በመፈፀም ጎሎችን ሲፈልግ ይታያል። ከእነዚህ አላማ ያላቸው የኳስ ቅብብሎች በተጨማሪ ቡድኑ ሳይታሰብ እያሳየ ያለው የፈጣን ሽግግሮች (ከመከላከል ወደ ማጥቃት) አጨዋወት ተጋጣሚን ሲያስደነግጥ ተስተውሏል። ከዚህ ውጪም ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ፈጣን እና ታታሪ ተጨዋቾች ጥረት ተጋባዦቹን ሊፈትን እንደሚችል አመላክቷል።
ኳስን ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ለመመስረት የሚጥሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተጋጣሚ አስጨንቆ ኳስ ለመቀማት ሲሞክርባቸው እንደሚቸገሩ በተደጋጋሚ ታይቷል። በዚህም ረገድ ተጋጣሚያቸው ሃዲያ ሆሳዕና የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች የቅብብል ስህተቶችን እንዲሰሩ ካስጨነቁ ለቡድናቸው በጎ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በነገው ጨዋታ የታፈሰ ሰለሞን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት እንደማያገኙ ተረጋግጧል።
ከሜዳቸው ውጪ ቀርቶ በሜዳቸውም አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብን አላማ አድርገው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። እስከ አራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሁለት ጎሎችን ብቻ ተጋጣሚ ላይ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ላይ በአራት ጨዋታዎች ያስቆጠረውን የግብ መጠን (2) በማስቆጠር የጠፋበትን የግብ ማግባት መንገድ ያገኘ ይመስላል። ይህም ለቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ላላቸው ተጫዋቾች የራስ መተማመን እንደሚያመጣ ይታሰባል።
የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ኳስን መሰረት ያደረገ መሆኑ ይህንን ለማጨናገፍ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በርከት ያሉ የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን እንደሚጠቀሙ ይገመታል። ይህ ውሳኔ ለኳስ ቁጥጥሩ ብቻ ሳይሆን አስተማኝ ላልሆነውን የቡድኑ የተከላካይ መስመር ሽፋን ለመስጠት ታስቦ እንደሚደረግ ይታሰባል። በተጨማሪም በፊት መስመር የሚገኙት ተጫዋቾች ከኳስ እና ያለ ኳስ እንቅስቃሴ ከግብ ክልሉ ኳስ መስርቶ የሚወጣው ቡናን የቅብብል ስህተቶች መጠቀም ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል። በአንፃራዊነት የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆነው የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀምም በገነው ጨዋታ ከሚገኙ የቆሙ ኳሶች ውጤት ይዘው ሊወጡ እንደሚችሉ ይገመታል።
የሊጉ አዲስ ክለብ ሀዲያ ከድሬዳዋ ከተማ በመቀጠል ብዙ ጎሎችን ያስተናገደ (9) ክለብ ነው። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ግብ ሊቆጠሩበት የሚችሉ ስህተቶችን ካልቀነሰ ችግሮችን ሊጋፈጥ ይችላል።
ቡድኑ በጉዳት በረከት ወልደዮሐንስ፣ እርቅይሁን ተስፋዬ ፣ መሐመድ ናስር እንዲሁም ሙሳ ካማራን በነገው ጨዋታ አያሰልፍም።
እርስ በእርስ ግንኙነት
ኢትዮጵያ ቡና እና ሃዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሁለቱንም ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
ተ/ማርያም ሻንቆ
አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አስራት ቱንጆ
ፍ/የሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሣ – አማኑኤል ዮሐንስ
አቤል ከበደ – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
አቤር ኦቮኖ
ፍራኦል መንግስቱ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቃታ
– ሄኖክ አርፊጮ
አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – ዮሴፍ ደንገቱ
ቢስማርክ አፒያ – ኢዮኤል ሳሙኤል – ቢስማርክ ኦፖንግ
© ሶከር ኢትዮጵያ