ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወነውን የስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ የተለያየው አዳማ አዳማ ከተማ በሁለተኛ ሳምንት ያሳካትን ድል በመድገም ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል።

ከወገብ በላይ እና ከወገብ በታች የተለያየ ቡድን እያስመለከተን አምስት ሳምንታትን የዘለቀው አዳማ ከኋላ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው እንደመሆኑ በቀላሉ ጎል ባይቆጠርበትም ጎል ለማስቆጠር በእጅጉ እየተቸገረ ይገኛል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ያላቸውን ጠባብ የማጥቃት አቀራረብ አማራጭ በማስፋት ሁነኛ ጎል የማስቆጠር መንገድን ማግኘትም ትልቁ የቤት ሥራቸው ነው።

ቡድኑ በነገው እለት የሚገጥመው በተመሳሳይ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካለውና ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ይበልጥ ጥብቅ አቀራረብ ያለው ጅማ አባ ጅፋር መሆኑ የጎል እድል ለመፍጠር እንደሚቸገር ይገመታል። ብዙም ክፍተት የማይሰጠውን ቡድን ለመስመር አማካዮች ወደ መስመር የተለጠጠ ሚና በመስጠት ለአጥቂዎች እና ከመሐል እየተነሳ ጥሩ የማጥቃች አማራጭ ለሚሆነው ከነዓን ማርክነህ ክፍተትን መፍጠር ላይ አተኩረው እንደሚጫወቱ ይገመታል።

በአዳማ በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በተቃራኒው ዐመለ ሚልኪያስ እና አማኑኤል ጎበና ተመልሰዋል።

ባለፈው ሳምንት የሊጉ የመጀመርያ ድሉን በማሳካት መነቃቃት ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውስጥ ይልቅ ከሜዳ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሁንም ፈተና ሆነውበታል። ቡድኑ በአምስተኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1 ከረታ በኋላ በማግስቱ የቡድኑ ሙሉ ተጫዋቾች ልምምድ አቁመው የነበረ ሲሆን የአራት ወራት ደመወዝ ክፍያ አለመከፈልም ይህን ውሳኔ ለመወሰን እንዳስገደዳቸው ተጫዋቾቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ያለፉትን አምስት ቀናት ከልምምድ የራቁት የክለቡ ተጫዋቾች እስከ አሁን የቡድኑ የበላይ አካላት መጥተው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረቶችን እንዳላደረጉ የገለፁ ሲሆን ይህን ዳሰሳ እስካጠናከርንበት ሰዓት ድረስ ክፍያ ያልተፈፀመ ቢሆንም የቡድኑ አባላት ወደ አዳማ መጓዛቸው ታውቋል።

ከደሞዝ አለመከፈል ጋር ከተያያዘው ችግር ባሻገር የውጪ ተጫዋቾቹን በሥራ ፈቃድ ምክንያት መጠቀም ያልቻለው የጳውሎስ ጌታቸው ቡድን ከችግሮች ጋር እየታገለ መልካም የሚባል አጀማመር አድርጓል ማለት ይቻላል። ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመሆኑ እና ሁለት የፕሪምየር ሊግ የሜዳው ጨዋታዎቹን ጨምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ያሳለፈበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ቤተኛ መሆኑ ጎል ለማስቆጠር ከሚቸገረው አዳማ ከተማ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ትልቅ ስንቅ ይሆነዋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ጅማ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው ሲሆን ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ እስካሁን ጅማ ላይ ድል ማስመዝገብ አልቻለም።

– በአራቱ ግንኙነቶች ጅማ 8 ሲያስቆጥር፤ አዳማ 1 ብቻ አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (3-5-2)

ደረጄ ዓለሙ

መናፍ ዓወል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ

ሱለይማን ሰሚድ – አዲስ ህንፃ – ብሩክ ቃልቦሬ – ከነዓን ማርክነህ – ሱሌይማን መሐመድ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ሄኖክ ገምቴሳ – ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ኤልያስ አህመድ

ጀሚል ያዕቆብ – ብዙዓየሁ እንደሻው – ኤርሚያስ ኃይሉ


© ሶከር ኢትዮጵያ