ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሀዋሳ ላይ የሚደረገውን የስድስተኛ ሳምንት ሌላው መርሐ ግብር እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ሀዋሳን በመርታት በሜዳው በመቐለ ከደረሰበት ሽንፈት በቶሎ ያገገመው ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ወደ ሰንጠረዡ አናት ይበልጥ ለመጠጋት አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

የዘርዓይ ሙሉ ስብስብ ለተጋጣሚ አስፈሪ ከሆኑ የአጥቂ መስመሮች አንዱ ነው። ነገ የሚገጥሙት ቡድን በተቃራኒው የሊጉ ደካማ የመከላከል ሪከርድ ያለው ድሬዳዋን መሆኑ ደግሞ በጨዋታው ምናልባትም በርካታ ጎሎች ልንመለከትበት የምንችለበት እንደሚሆን ይገመታል።

በፊት መስመር የሚሰለፉት አዲስ፣ ሀብታሙ እና ይገዙ ፍጥነት፣ የመዋለል ባህርይ እና የአጨራረስ ብቃት ላይ ተመረኮዘው ቡድኑ በነገው ጨዋታም በእነዚሁ ተጫዋቾች ላይ ያመዘነ አጨዋወትን ይዞ መግባቱ አይቀሬ ነው። ከተጋጣሚው ባህርይ አንፃር በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የሚወስድ ከሆነ ደግሞ ዳዊት ተፈራ ላይ አተኩሮ መሐል ለመሐል ማጥቃትን ምርጫው ሊያደርግ ይችላል።

ሲዳማ ከማጥቃት ጥንካሬው በቃራኒው በእያንዳንዱ ጨዋታ ግብ የተቆጠረበት የተከላካይ መስመሩ ደካማ ጎኑ ነው። በመልሶ ማጥቃት ለጨዋቻው እንደሚቀርብ የሚጠበቀው ድሬዳዋ ከተማን ድንገተኛ ጥቃቶች የመከላከል አቅማቸውም በነገው ጨዋታ ይፈተናል።

በቡድኑ በኩል ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ጉዳት ላይ ሲሆን ዮናታን ፍሰሀ በጉዳት መሰለፉ አጠራጥሯል፡፡

የስምዖን ዓባይ ቡድን ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት እየተጣጣረ ይገኛል። ከባህር ዳር የ4-1 ሽንፈት በኋላ ከቡና ጋር አቻ የተለያየው ቡድኑ ነገ ሲዳማን በመርታት ለዓመታት ደካማ ጎኑ ከሆነው ከሜዳ ውጪ የማሸነፍ ችግር ለመላቀቅ አልሞ ለጨዋታው ይቀርባል።

በርካታ ጎሎችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው እየተነቃቃ የመጣው ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ ጎል ሳያስተናግድ መውጣቱ በመከላከሉ ረገድ መሻሻል ለማሳየቱ ፍንጭ ቢሰጥም የወሳኝ ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ጉዳት በድጋሚ ስጋት ውስጥ የሚከተው ነው።

ቡድኑ ነገ የሚገጥመው በፈጣን የመስመር ሽግግር የሚያጠቃውና ከመስመር እየተነሱ የሚያጠቁ አጥቂዎችን በመሆኑ በቦታው ላይ ትኩረት አድርጎ የመሮጫ እና የመቀባበያ ቦታዎችን መዝጋት ተቀዳሚ አላማ እንደሚሆን ይጠበቃል። በተጨማሪም የሲዳማ ደካማ ጎን የሆነው የተከላካዮች የመናበብ ችግርን በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር መሞከር ከነገው ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። የቡድኑ ግዙፍ አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎም በነገው ጨዋታ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ እንደመጫወቱ ይህንን አጥቂ አላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች ለተጨዋቹ ስለሚላኩ ከቡድን አጋሮቹ በበለጠ የሚገኙ ጥቂት አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም አለበት። (ቡድኑ በሊጉ ካስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች መካከል ሁለቱ መነሻቸው ከቆመ ኳስ መሆኑ ልብ ይሏል)

በብርቱካናማዎቹ በኩል ምንያህል ተሾመ፣ አማኑኤል ተሾመ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና በረከት ሳሙኤል በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ወደ ሀዋሳ ያመራው ሳምሶን አሰፋም መሰለፉ አጠራጥሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት

በሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ14 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና በ7 ድል ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ 1 ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ግንኙነቶች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በ14 ግንኙነቶች ሲዳማ 14 ጎሎች ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 6 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ጊት ጋት – ግሩም አሰፋ

አበባው ዮሀንስ – ብርሀኑ አሻሞ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – አዲስ ግደይ

ይገዙ ቦጋለ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ (አ)

ፍሬዘር ካሣ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል – አማረ በቀለ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ