ጉዳት ላይ የሚገኙት ሦስት የወልዋሎ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የሚመለሱበት ቀን ታውቋል።
በሊጉ ውስጥ የተጫዋቾች ጉዳት ካጠቃቸው ቡድኖች አንዱ የሆኑት ወልዋሎዎች ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ማጣታቸው ይታወሳል። ባሳለፍነው ሳምንት አምበሉ ዓይናለም ኃይለ፣ ከወላይታ ድቻ ጋር በነበረው ጨዋታ ደግሞ ጋናዊው አቼምፖንግ አሞስን ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ያጡት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ለቀጣይ ሁለት ወይም ሦስት ጨዋታዎች የካርሎስ ዳምጣውን ግልጋሎት አያገኙም።
ስሑል ሽረን 3-0 ባሸነፉበት ጨዋታ የጎን አጥንት ስብራት ገጥሞት ባለፉት ጨዋታዎች ያልተሰለፈው ተከላካዩ አቼምፖንግ አሞስ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ከጉዳቱ በማገገም ሲገኝ ከሰባተኛ ሳምንት በኋላ በግሉ ቀለል ያለ ልምምድ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል።
ሌላው ባለፈው ሳምንት በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከተጫዋች ጋር ተጋጭቶ ጉዳት የደረሰበት ዓይናለም ኃይለ ከስድስት እስከ ሰባት ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ተረጋግጧል። በሜዳ ውስጥ ከሚሰጠው ግልጋሎት በተጨማሪ ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ በአምበልነት ሲመራ የቆየው ይህ ተጫዋች በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይገመታል።
ሦስተኛ በቡድኑ ጉዳት ዝርዝር የገባው ካርሎስ ዳምጠው ከገጠመው ጉዳት አገግሞ ቡድኑ መቐለን ሲገጥም ወደ ሜዳ ተመልሶ የነበረ ቢሆንም ጉዳቱ በድጋሚ በማገርሸቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ከሜዳ ይርቃል። በበርካታ ቦታዎች ተሰልፎ የተጫወተው ካርሎስ ደምጠው በአራት ጨዋታዎች ሶስት ግቦች ማስቆጠሩ ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ