የአዴት ከተማ ተጫዋቾች የመኪና አደጋ ደረሰባቸው

ነገ ጨዋታ ለማድረግ በጉዞ ላይ የነበሩት የአዴት ከተማ ተጫዋቾች ረፋድ ላይ አደጋ አጋጥሟቸዋል።

በአማራ ክልል ሊግ የሚሳተፉት አዴት ከተማዎች ነገ ላለባቸው የምድብ የመክፈቻ ጨዋታ ነበር ጉዞ ሲያደርጉ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው። ትላንት ከአዴት ወደ ገንደ ውሃ ጉዟቸውን የጀመሩት የቡድኑ አባላት ሃይከል (የጭልጋ ወረዳ ዋና ከተማ) ላይ ካደሩ በኋላ ማለዳ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ቡድኑን የያዘው መኪና 12 ሰዓት ከኬላ ፍተሻ ተፈትሾ ከተነሳ በኋላ 1 ሰዓት ላይ አደጋ አጋጥሞታል።

የቡድኑ ልዑካን ሃይሩፍ በተባለ መኪና ጉዛቸውን ሲያደርጉ እንደነበረ እና በመኪና ውስጥ 24 ሰዎች (21 የቡድኑ አባላት፣ የመኪናው ሹፌር፣ ረዳት እና አንድ መኪናውን ሊሸኝ አብሮ የወጣው የመከላከያ ሰራዊት አባል) እንደነበሩ ተነግሯል።

በአሁኑ ሰዓት የመኪናውን ሹፌር ጨምር አራት ሰዎች ከባድ አደጋ አጋጥሟቸው ጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል እንደሚገኙ ታውቋል። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን መጠነኛ ጉዳት ብቻ እንደደረሰባቸው እና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

* ሶከር ኢትዮጵያ በቡድኑ ላይ በደረሰው አደጋ ተሰማውን ሀዘን እየገለፀ የተጎዱ የቡድኑ አባላት በፍጥነት እንዲያገግሙ መልካሙን ይመኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ