የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 ጅማ አባ ጅፋር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ አሰልጣኞቹ የሚከተለውን ብለዋል።

👉 “በተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ አይደለም ሳናሸንፍ የወጣነው” ደጉ ዱባም (አዳማ ከተማ – ምክትል አሰልጣኝ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በጨዋታው ብዙ ለማጥቃት ሞክረናል። ነገር ግን ያገኘናቸውን እና የፈጠርናቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀምንም። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ሜዳ ላይ በመሆን አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረን ነበር። ነገር ግን የጨዋታ ዋነኛ አላማ ግብ ማስቆጠር ነውና እኛ ግብ ሳናስቆጥር ወጥተናል።

ነጥብ ሳትይዙ የወጣችሁት በእናንተ ድክመት ነው ወይስ በተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ?

በተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ አደለም ሳናሸንፍ የወጣነው። እኛ በፈጠርነው የአጨራረስ ችግር ነው ጨዋታውን ሳንገድል የወጣነው።

ስለ ተጫዋቾቻቸው እንቅስቃሴ?

ያሰብነውን ተጨዋቾቻችን ለመተግበር ሞክረዋል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ አይደለም። ወደ ሜዳ ስንገባ ሦስት ነጥብን አስበን ነበር የገባነው። እግር ኳስ ስለሆነ ምንም ማድረግ አንችልም። ቡድናችን በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። በሊጉ ላይ ካሉ ክለቦች ምንም ጨዋታ ያልተሸነፈው ክለብ አዳማ ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንን ያሳያል። በቀጣይ ግን በተለይ ፊት አካባቢ ያሉብንን ችግሮች ቀርፈን ለመቅረብ እንሞክራልን።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴ?

እነሱ መሐል ላይ በጣም ተጠቅጥቀው ስለነበር እኛ ወደ መስመሮች እየወጣን ለመጫወት ሞክረናል። በዚህም ብዙ ኳሶችን ወደ መስመር እያወጣን ለማሻማት እና በግምባር ለማስቆጠር ጥረናል። ነገር ግን አልተሳካልንም። እነሱ መሃሉን ዘግተውታል ለመከላከል ነው ወደ ሜዳ የገቡት።

👉 “በእግር ኳስ አግባብ ቢሆን ኖሮ ይህንን ጨዋታ ማድረግ አይኖርብንም ነበር።” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባጅፋር)

ስለ ጨዋታው?

ባሳለፍነው ሳምንት ከተጫወትኩበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በኋላ ወደ ሜዳ ስገባ ዛሬ የመጀመሪያዬ ነው። ተጨዋቾቼ በጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እስካሁን ልምምድ አልሰሩም ነበር። አዳማም የገባሁት ትላንትና ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ነው። ነገር ግን ዛሬ ተጨዋቾቼ ላይ ያየሁት ፍላጎት በጣም አስገርሞኛል። በዚህም ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ። ተጨዋቾቼ የሚፈልጉት ነገር ከተስተካከለላቸው ምንም ነገር ለማምጣት እንደማይቸገሩ አይቻለሁ። በሁለተኛው አጋማሽም አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። በአጠቃላይ ግን ካለ ልምምድ እንደመምጣታችን በጥሩ ሁኔታ ተጫውተናል።

ወደ ሜዳ ይዘውት የገቡት እቅድ?

ዛሬ እኛ ስለ ቴክኒክ እና ታክቲክ ብሎም ስለ ማጥቃት እና አለማጥቃት አናወራም። ቀድሜ እንደገለፅኩት ከጊዮርጊስ ጨዋታ በኋላ ምንም ልምምድ አላደረግንም። ስለዚህ ዛሬ ተጨዋቾችን ምንም መውቀስ አልችልም። በእግር ኳስ አግባብ ቢሆን ኖሮ እንደውም ይህንን ጨዋታ ማድረግ አይኖርብንም ነበር። ነገር ግን ተጨዋቾቼ የምነገርራቸውን ነገር ሰምተው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘን ወተናል።

ስለ ሰዒድ ሀብታሙ ብቃት?

ሰዒድ እንዳያችሁት በጣም ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው። ከእሱ በተጨማሪም በተጠባባቂ ወንበር ላይ በጥሩ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ዘሪሁን አለ። በተጨማሪም መሐመድ ሙንታሪ አለ። ስለዚህ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ምንም የምሰጋበት ነገር የለም።

የፓስፖርት ጉዳይ ያልተጠናቀቀላቸው የውጪ ሃገር ተጨዋቾች?

እኔ ስለእሱ አላውቅም። ከላይ ያሉት ፈርመው ሲያመጡልኝ ብቻ ነው ተጨዋቾቹን ወደ ሜዳ የማስገባቸው። ያለበለዚያ ባለተጨበጠ ነገር ኃላፊነት ወስጄ ተጨዋቾቹን ወደ ሜዳ አላስገባም።


© ሶከር ኢትዮጵያ