ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ የዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድልን አሳካ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ጋብዞ 2ለ1 ተሸንፏል። የምስራቁ ክለብም የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድሉን አስመዝግቧል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች በአምስተኛው ሳምንት ሀዋሳን ካሸነፈው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሚካኤል ሀሲሳን ተቀዳሚ ተመራጭ በማድረግ በዳዊት ተፈራ ሲተኩ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተው የመጡት ብርቱካናዎቹ በበኩላቸው በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርገው ጀምረዋል፡፡ ሳምሶን አሰፋን በፍሬው ጌታሁን፣ በረከት ሳሙኤልን በያሬድ ዘውድነህ፣ አማኑኤል ተሾመን በዘሪሁን አንሼቦ፣ ሳሙኤል ዘሪሁንን በፍሬድ ሙሸንዲ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

ጨዋታው ገና ከጅምሩ የሲዳማ ቡና አስፈሪ የማጥቃት ኃይል የተስለዋለበት ሲሆን በዚህም 2ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። የድሬዳዋን የተከላካይ ክፍል ክፍተት የተመለከተው አማካዩ አበባየው ዮሐንስ መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አምበሉ አዲስ ግደይ ብልጠቱን ተጠቅሞ ኳሷን ከመረብ በማሳረፍ ቡናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓቸዋል፡፡

ለወትሮው ከሚታወቁበት ረጃጅም ኳሶች በዛሬው ጨዋታ ቅብብልን መሰረት በማድረግ ለመጫወት ያለመ እንቅስቃሴ ያደረጉት ሲዳማዎች ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን ከአማካዮቹ ወደ አጥቂዎች በፍጥነት በሚሸጋገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም አምበሉ አዲስ ግደይ ተደጋጋሚ እያገኘ መረጋጋት ባለመቻሉ በቀላሉ ሊባክኑበት ችለዋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማዎች በተቃራኒው ያገኟቸውን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ውጤታማ ነበሩ። 13ኛው ደቂቃም ከመሐል ሜዳ በግራ በኩል ባጋደለ ቦታ ላይ ያገኙት ቅጣት ምት በረጅሙ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ተሻምቶ የተከላካዮቹ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግንባሩ ጨረፍ አድርጎ ከመረብ በማሳረፍ ብርቱካናማዎቹን አቻ አድርጓል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ አጀማመራቸው ለመመለስ እና ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ድሬዳዋ ግብ ክልል ደርሰዋል፡፡ 15ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል አማኑኤል እንዳለ ያሻገራትን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በግንባር ገጭቶ የግብ የላይኛው ቋሚ ሲመልስበት በድጋሚ ስትመለስ አዲስ ዳግም አግኝቷት በተመሳሳይ በግንባር ገጭቶ በግቡ ቋሚ ስር ታካ ወጥታለች፡፡

ደቂቃው እየገፋ በመጣ ቁጥር ድሬዳዋ ከተማዎች ገና በጊዜ አንድ ነጥብን ፍለጋ በሚመስል መልኩ ሰዓት ለማባከን ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ ሲወድቁም መመልከት ችለናል፡፡ ሆኖም የእለቱ ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ በዝምታ ለማለፍ ሲሞክሩ አራተኛ ዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ ዳኛውን በመጥራት ማስጠንቀቂያ እንዲመለከቱ ሲያስደርጉ ታይቷል፤ በዚህም ሂደት ስድስት የድሬዳዋ ተጫዋቾች ቢጫ ካርድን ተመልክተዋል፡፡ 23ኛው ደቂቃ አበባየው ዮሀንስ አሁንም የድሬዳዋ ተከላካዮችን የአደራደር ስህተትን አይቶ የሰጠውን አዲስ ግደይ ወደ ግብ ይዞ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ፍሬው እንደምንም አድኖበታል፡፡ በጭማሪ የእረፍት መውጫ ሰዓትም ሲዳማ ቡናዎች በአማኑኤል እንዳለ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሯል፡፡

ከእረፍት መልስ ሲዳማ ቡና አማካይ ቦታውን በደንብ ለመጠቀም በማሰብ ልምድ ያለውን ዳዊት ተፈራን በማስገባት ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ሚካኤል ሀሲሳ የለወጠ ቢሆንም ከመጀመሪያው አጋማሽ አማዛኙን የሚቆራረጡ ኳሶችን የበዙበት ሲሆን በአንፃሩ ድሬዳዋዎች ከአማካይ ስፍራ ዋለልኝ ገብሬን አስወጥተው ቢኒያም ጥዑመልሳንን በመተካት የአደራደር ሽግሽግ አድርገው ይበልጥ ወደ መከላከሉ አመዝነዋል።

የድሬዳዋን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ሲቸገሩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች 64ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ የግብ ጠባቂው ፍረው ጌታሁንን አቋቋም አይቶ የመታት ኳስ የላይኛው ብረቱ የመለሰበት አስቆጪ ሙከራቸው ነበረች፡፡

66ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ግብ ሲያስቆጥሩ ጨዋታውም ለሦስት ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር። የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች በድሬዳዋ የግብ ክልል ኳስን ይዘው ባሉበት ወቅት የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ አያሌው አሰፋ ከጨዋታ ውጪ ብለው ባንዲራቸውን ባነሱበት ቅፅበት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጪ መስሏቸው ቢቆሙም ከድሬዳዋ ተከላካዮች የተለጋችው ኳስ በቀጥታ የሲዳማ የግብ ክልል አምርታ ያሬድ ታደሰ ተቆጣጥሮ ያመቻቸለትን ፍሬድ ሙሸንዲ አግኝቶ ወደ ግብነት በመለወጥ እንግዳዎቹን መሪ አድርጓል፡፡

ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ረዳት ዳኛው ምልክት አሳይቶ የመሀል ዳኛው ሳይመለከት እንዳለፈው በመግለፅ ተቃውሞ ቢያሰሙም የእለቱ ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ ግቧን አፅድቀዋታል፡፡ ሲዳማ ቡናዎችም ቅሬታቸውን በአምበሉ አዲስ ግደይ አማካኝነት በክስ መልክ ካስመዘገቡ በኃላ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

ሲዳማዎች በተደጋጋሚ ከተሻጋሪ እንዲሁም በቅብብል ወደ ሳጥን ተጠግተው በመጫወት በርካታ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በዕለቱ ድንቅ የነበረው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ሲያድናቸው ውሏል፡፡ 90+2 ላይ ደግሞ የድሬዳዋ ተከላካዮች በአዲስ ግደይ ላይ በሰሩት ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ቢመታውም ፍሬው ጌታሁን አድኖበት ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች በተለይ አዲስ ግደይ እና ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በዕንባ ከሜዳ ወጥተዋል፡፡

✿በጨዋታው ከእለቱ ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ ይልቅ አራተኛ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ስራ በዝቶበት ውሏል። በተለይ ዋና ዳኛው በዝምታ የሚያልፏቸው ውሳኔዎች ላይ ጨዋታውን እያስቆሙ ዋና ዳኛውን በመጥራት ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ጥቆማ ሲሰጥ አይተናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሁለቱም ቡድን ቴክኒክ ቦታ ላይ ያሉት ሲቆጣጠሩ የነበረት ሂደትም ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን አይተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ