ሪፖርት | ወልቂጤ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው ባደረገው ጨዋታ ከሽረ ነጥብ ተጋርቷል

በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ጨዋታቸውን ያከናወኑት ወልቂጤዎች ስሑል ሽረን አስተናግደው 0-0 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

በጨዋታው ሠራተኞቹ ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው ከአዳማ ከተማ አቻ ከወጡበት ስብስባቸው በረከት ተሰማ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ዓብዱሰላም አማን እና ሙሉዓለም ረጋሳን በዮናስ ግርማይ ፣ ክብሮም ብርሃኑ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ሸዊት ዮሐንስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና በርካታ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ ወልቂጤዋች ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ ስሑል ሽረዎች በተለመደው የመስመር አጨዋወት ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። እንግዶቹ በመጀመሪያው ደቂቃ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል በመድረስ ብሩክ ሃዱሽ ከርቀት ባደረገው የግብ ሙከራ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩ ሲሆን በመስመር በሚሻሙ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ አደጋ ክልል ቢደርሱም በመጀመሪያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

በአንፃራዊነት በሦስተኛው የሜዳ ክፍል መቆየት የቻሉት ባለሜዳዋቹ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አጀማመር አድርገው በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎችን ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተለይም ምንተስኖት አሎ ከመስመር የተሻገረችን ለግብ የቀረበች ኳስ ያዳነበት ቅፅበት እንዲሁም ጫላ የተሻ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት ለጥቂት የወጣችው እና ጃኮ አረፋይ በሁለት አጋጣሚዎች ያገኛቸው ወርቃማ ዕድሎች በባለሜዳዎቹ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ።

እንግዶቹ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ሲከላከሉ በተቃራኒው ወልቂጤዎች በቁጥር በርካታ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የአሸናፊነት ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወት የቻሉበት ሁለተኛው አጋማሽ በሽረዋች በኩል ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ነበር። ሽረዎች በአብዱልለጢፍ ማሀመድ አማካይነት በመልሶ ማጥቃት በ51ኛው እና 68ኛው ደቂቃ ከሰነዘሩት ጥቃት ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። በተቀራኒው ወልቂጤዋች በሁለተኛው አጋማሽ እጅጉን ተጭነው የተጫወቱት ሲሆን ጃኮ አረፋት በ76ኛው ደቂቃ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ያገኘውን የግብ አጋጣሚ በደርቱ አብርዶ ወደ ግብ ለወጠው ቢባልም የሽረ ተከላካይ ፈጥኖ ደርሶ ያወጣበት አጋጣሚ ቡድኑን ባለድል ለማድረግ የተቃረበ ነበር። አብዱልከሪም በ63ኛው ደቂቃ መትቶት ምንተስኖት አሎ በጥሩ ብቃት ያዳነበት እንዲሁም ሙሀጅር መኪ ፣ ሄኖክ አወቀ እና አቤኔዜር ኡቴ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ተጠቃሽ ነበሩ። አህመድ ሁሴንም ከመሀል የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም በጠንካራነቱ የሚነሳ ነበር።

ሆኖም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች ሦስተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤት ሲያስመዝግቡ ባለሜዳዎቹም ከሁለት ጨዋታ አራተኛ ነጥባቸውን ሰብስበዋል።

* በጨዋታው የስሑል ሽረ ቡድን አባላት የዳኛን ውሳኔ በተደጋጋሚ ሲቃወሙ የታዩ ሲሆን በተለይም ምክትል አሰልጣኙ መብራቶም ፍስሀ በሚያሳዩት ተደጋጋሚ ተቃውሞ የዕለቱ ዳኛ የቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ለማረጋጋት ሞክረዋል።


በዕለቱ በስታዲየም ከታዩ መልዕክቶች መካከል..


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ