ሪፖርት | ዐፄዎቹ ባህር ዳርን በመርታት ሊጉን መምራት ጀምረዋል

በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ ጎንደር ላይ ባህርዳር ከተማን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል።

በጨዋታው መጀመሪያ ከከፍተኛ ሊግ እስከ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማን ያገለገለው የአሁኑ የባህር ዳር አማካይ ፍፁም ዓለሙ (ኤፍሬም) የራሱን ምስል የያዘ የፎቶ ግራፍ ስጦታ በደጋፊ ማኅበሩ ተበርክቶለታል።

ዐፄዎቹ ባለፈው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር 3 አቻ የተለያየውን ስብስብ ያለምንም ቅያሪ ይዘው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በእንግዳዎቹ በኩል ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሁለት አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ በክፍያ ምክንያት ልምምድ ባቆሙት ሀሪሰን ሄሱ ፣ አዳማ ሲሶኮ እና ማማዱ ሲድቤ ምትክ ፅዮን መርዕድ፣ አቤል ውዱ እና ስንታየሁ መንግስቱ የመሰለፍ ዕድል ያገኙ ሲሆን ዳንኤል ኃይሉን በማሳረፍም ሳምሶን ጥላሁንን በመጀመሪያው አሰላለፍ አካተዋል።

ተመጣጣኝ እና ማራኪ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ እስከ 10ኛው ደቂቃ ድረስ መሀል ሜዳ ላይ የመዘነ ነበር። በ11ኛው ደቂቃ ግን ሽመክት ላይ በተሰራ ጥፋት በተገኘ የቅጣት ምት ሱራፌል ወደግብ አክርሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ያወጣበት ቀዳሚ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ኳስ ወደ ማዕዘን ምት አምርቶም የተሻማውን ኳስ ኦሴይ ማውሊ በጭንቅላት ገጭቶ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹን መሪ አድርጓል።

ፋሲሎች ከግቡ መቆጠር በኋላ ጨዋታውን በማቀዝቀዝ እና የባህርዳርን እንቅስቃሴ በመገደብ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳያስተናግዱ መወጣት ችለዋል። በሙከራ ደረጃ 15ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት መሀል ሜዳ ላይ ያገኘውን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ወደግብ የመታው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር ። 30ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሙጂብ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ አድኖበታል። በተጨማሪ በ38ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ አክርሮ የመታውን ኳስ ሙጅብ ቃሲም በጭንቅላቱ ለማግባት ሞክሮ አሁንም ፅዮን ሊያመክንበት ችሏል።

ባህር ዳሮች በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ታይተዋል። በግራ መስመር ወሰኑ ዓሊ ኳስ እየነዳ ወደ ፋሲል ከነማ የተከላካይ ክፍል በሚጠጋበት ወቅት ተደጋጋሚ ጥፋቶች ሲፈፅሙበት እንዲሁም በርካታ የማዕዘን ምቶችም ሲገኙ የነበረ ቢሆንም ባህርዳር ከነማዎች የቆሙ ኳሶችን መጠቀም ተስኗቸው ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ባህርዳር ከነማዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል 22ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ዓሊ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። 29ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካዮች ቀድሞ በመሮጥ ስንታየሁ መንግሥቱ ያገኘውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂ አድኖበታል። ባህር ዳሮች ከሳጥን ውጪ ኳሶችን ወደ ግብ በመምታት ግብ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት የፋሲል ከነማን ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬን ሲፈትን ተስተውሏል። ከነዚህም ውስጥ 42ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከርቀት ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ድንቅ የሚባል ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽም ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ባህር ዳሮች ከመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸውን የግብ ማግባት ከፍተት ባለማስተካከላቸው በርካታ ሙከራዎች ቢያደርጉም ግብ ማስቆጥር ሳይቻላቸው ቀርቷል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተመታን ኳስ ሚካኤል ሳማኪ ወጥቶ በጭንቅላቱ ሲጨርፍ ከሳጥን ውጪ ፍፁም ዓለሙ እና ግርማ ደሲሳ በተከታታይ ያደረጉት ሙከራ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የቀረበ ነበር። በድጋሚ 49ኛው ደቂቃ ላይ የግርማ ደሲሳ እንዲሁም 52ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የቀድሞ ክለቡን የሚገጥመው ፍፁም አለሙን ጥረቶች ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው ሚኬል ሳማኬ አድኖባቸዋል። በተጨማሪም 62ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግስቱ ከግብ ጠበቃ ጋር ተገናኝቶ ሰዒድ ሀሰን ከኋላ ተንሸራቶ ያዳነበት እና 83ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ወርቁ ከቅጣት ምት ደረጀ ወርቁ ያሻማውን ኳስ በጭንቅለቱ በመግጨት ወደ ግብ የሞከረው እና በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ለፋሲል ተካልኝ ቡድን የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ጥሩ ባልነበሩበት አጋማሽ ግብ ከማስቆጠር ያልተገደቡት አየዐፄዎቹ የአጥቂ ክፍላቸውን ጥንካሬን ያሳዩ ሲሆን የተገኙትን አጋጣሚዎችን ወደ ግብ በመቀየር መሪነታቸውን አጠናክረው ወጥተዋል። ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሸ ኢላማውን የጠበቀው የመጀመሪያው ሙከራው ወደ ግብነት የተቀየረ ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ ከበዛብህ መለዮ በጥሩ ዕይታ የተሻማውን ኳስ ኦሲ ማውሊ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ያሰፉት ፋሲሎች ከሌላው ጊዜ ባነሰ መልኩ ሜዳ ላይ የነበራቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ ተገድቦ ተስተውሏል። ያም ቢሆን 74ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማውሊ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻገረለትን በጭንቅላቱ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት እና 86ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከርቀት ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የቡድኑ ጠንካራ ሙከራዎች ነበሩ። በመጨረሻም ዐፄዎቹ 90ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠረው ጎል ጨዋታውን በ3-0 ውጤት መደምደም ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ 11 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ሲችል ባህርዳር ከተማ ደግሞ 7ኛ ደረጃ ላይ ለመገኘት ተገዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ