የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-2 ድሬዳዋ ከተማ

በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና በሜዳው በድሬዳዋ ከተማ ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርተዋል፡፡

👉 ” ትልቁ ነገር ሦስት ነጥቡ እንጂ የወረደ ጨዋታ መጫወታችን አይደለም” ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

“ያው እንግዲህ እንዳያችሁት በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶብናል። ሆኖም ግን አሁንም ከነበርንበት ሁኔታ ለመውጣት ይዘን የገባነውን ታክቲክ ለመተግበር አስበን በተወሰነ መልኩ ተግብረን መውጣት ችለናል፡፡ አንድነታችን ነው ውጤቱ ሊያመጣ የቻለው እንጂ እንደ ኳስ ቁጥጥር እና ከእረፍት በፊት እንዳገኙት የጎል ዕድል እና አጋጣሚ መጠቀም ቢችሉ ኖሮ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችል ነበር። ቢሆንም ግን ማድረግ ያለብንን በተለይ ከእረፍት በኋላ ተደራጅተን ለመከላከል አስበን ያንንም ተግባራዊ አድርገን ተሳክቶልናል፡፡

እንደኳስ እንቅስቃሴ ሲዳማ ቡና ጥሩ ነበር፤ በተለይ ከእረፍት በፊት። እንደ ውጤት እኛ ይዘን ለመሄድ ያሰብነው የሚካድ ነገር አይደለም፤ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዤ ለመሄድ ነበር ያሰብኩት። እንደልጆቼ ልፋት እና ጥረት ግን ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለናል፡፡ የልጆቼ ልፋት እንጂ እድለኝነት አይደለም፡፡

ስለ ሁለተኛዋ አጨቃጫቂ ግብ

“አወዛጋቢ የነበረው ሁለተኛው ግብ ብቻ ሳይሆን ፍፁም ቅጣት ምቷም ጭምር ነው፡፡ ይህ የዳኛ ውሳኔ ነው፤ ከዚህ በፊትም ብዙ ስህተቶች ይሰራሉ፡፡ ስህተት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ እሱን የሚያውቀው ዳኛው ነው፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱም ስህተት መሆን አለመሆኑን ዳኛው ነው የሚያውቀው። ስለዚህ ዘጠና ደቂቃ ካለቀ በኃላ ይሄ ይሄ ነው ብዬ ስለ ስህተት አልናገርም፡፡

በደካማ እንቅስቃሴ ስለማሸነፍ

“ዓለም ላይ ብዙ የወረደ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች አሉ፤ ስለ ሦስት ነጥቡ ብናወራ ይሻላል፤ ሲዳማ ቡናን በሜዳው መጥተህ ማሸነፍ። ቡድንህ ወረደ አልወረደ ይሄ ምንም የሚያሳይ አይደለም። በመልሶ ማጥቃት እኛ ጥሩ ነን። እንዴት እንደታየ አላውቅም እንጂ በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ነን። ኳስ በሜዳችን በማንሸራሸርም ጥሩ ነበርን። ዋናው ግን ትልቁ ነገር ሶስት ነጥብ ነው እንጂ የወረደ ጨዋታ መጫወታችን አይደለም፡፡


👉 “(ድሬዳዋዎች) በጣም ዕድለኞች ናቸው፤ እጅግ በጣም” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

ዛሬ አልታደልንም ማለት ይቻላል፤ በተለይ የአጨራረስ ችግር በሰፊው የታየበት ነው። በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ነበር የዋልነው፤ መጠቀም ግን አልቻልንም። ያው እግር ኳስ ነው፤ አንዳንዴ እንደዚህ ጥሩ ሆነህም ትሸነፋለህ። ኳስን በአግባቡ ሳይቀባበሉ ሲያሸንፉህ በጣም ያናድዳል፤ ያበሳጭማል፡፡ ግን ኳስ ነው ትቀበላለህ።

ከእረፍት በፊት ከአምስት ጎል በላይ ማግባት ነበረብን። ይህ ነው ዋጋ ያስከፈለን። አንዳንዴ እንዲህ አይነት እድሎችን ካልተጠቀምክ መጨረሻህ መሯሯጥ ነው የሚሆነው። የዛሬው ጨዋታ ትልቅ ትምህርት ሰቶናል ብዬ አስባለሁ። ዛሬ ነው የአጨራረስ ችግር የታየብን፤ ከዚህ ቀደም እነኚሁ አጥቂዎች ግን ሦስት ሦስት ግቦችን አግብተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በደንብ የሚስተካከል ነገር ነው፡፡

እነሱ ዕድለኞች ናቸው ምክንያቱም እግር ኳስ ማለት ይሄ ሁሉ ገብቶ ሚያየው ኳስን ነው፡፡ በረኛ ይጠልዛል፤ አንድ አጥቂ ይሮጣል፡፡ ይሄ ግን እግር ኳስ አይደለም በጣም ዕድለኞች ናቸው፤ እጅግ በጣም፤ ይሄን ደግሞ በዕርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡

ስለ ሁለተኛዋ ጎል

ረዳት ዳኛው አንስቷል፤ ረጅም ሰዓት አንስቶ ነበር፤ ስለዚህ ዳኛው አይቶ ማስቆም ነበረበት። ካልሆነ ደግሞ ጨዋታው ከጨዋታ ውጪ አይደለም የሚል ከሆነ ደግሞ ፍፁም ቅጣት ምት ነበር። ከሁለት አንዱ ነበር መሰጠት የነበረበት። ይህን ሁሉ ህዝብ ወዳልተፈለገ ስሜት የሚከተው ዳኝነት ነው፡፡ በጣም ትልቅ ስህተት ነው፤ ሁለተኛ የገባው ጎል ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ረዳት ዳኛው ካነሳ ደግሞ እስከ መጨረሻው ማንሳት፤ አንስቶ መቆም ልክ ጎል ከገባ በኋላ ማውረድ ማለት በጣም ያስጠይቃል፡፡ በዚህ ላይ ቪዲዮም ስለተቀረፀ ፌድሬሽኑ ምን እንደሚወስን የምናይ ይሆናል፡፡

የማጥቃት እና መከላከል አለመጣጣም

ጅምሩ ላይ በተፈጠረ ነገር ነው ይሄ ሊሆን የቻለው። ከኃላ መስመር ላይ የነበሩ ጠንካራ ልጆች ለቀውብናል፡፡ በዛ ቦታ ላይ ተተኪም አላገኘንም። ባሉት ተጫዋቾች ነው እያሸጋሸግን ያለነው። ምንም ጥርጥር የለውም የኃላ መስመራችን ላይ ክፍተት አለ። ያው አንደኛው ዙር እስኪያልቅ ባሉት ተጫዋቾች እንሸፍንና ለሁለተኛው ዙር ሌላ የቤት ስራ እንዳለን ነው የሚሰማን።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ