በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ እና ስሑል ሽረ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
👉 “ተጫዋቸቼ ጨዋታውን በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ለደጋፊዎቻችን ለመስጠት ያቅማቸውን ጥረዋል” ደግአረግ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው
” ውጤቱ ጨዋታውን አይገልፀውም። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎች በመፍጠሩም ሆነ በእንቅስቃሴ እኛ የተሻልን ነበርን። ሆኖም እግር ኳስ ነውና ውጤቱን በፀጋ እቀበለዋለን።
ጨዋታውን በሜዳችን እንደመጫወታችን ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ልጆቻንን ብዙ ጥረዋል። ይህን ውብ ደጋፊ ሙሉ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ለማስደሰት ተጫዋቾቻችን ያቅማቸውን ጥረዋል። ተጋጣሚያችን ይዞት የመጣው አቀራረብ ሙሉ ለሙሉ መከላከል ነበር። በአጋጣሚ ወደፊት የሚጣሉ ኳሶችን ለመጠቀም ቢያስብም ይህ ነው የሚባል አደጋ አልፈጠሩም ነበር።”
የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታ
” ከጠዋት ጀምሮ በከተማዋ የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ አስደሳች ነበር። እንግዳውን ቡድን ከመቀበል አንስቶ በደጋፊው የተሰሙት ህብረዜማዋች እጅግ ውብ ነበሩ። ልጆቻንን ይህን ጨዋታ በማሽነፍ ሦስት ነጥብ ለደጋፊዎቻችን ለመስጠት ያቅማቸውን ጥረዋል። በቀጣይ ከደጋፊው ጋር በመሆን ወደፊት እንጓዛለን። ስለነበረው አደጋገፍ እና ለታየው ስፖርታዊ ጨዋነት በቡድኑ ሥም አመሰግናለው።”
👉 ” በጨዋታው ለመተግበር ያሰብነውን እቅድ ተጫዋቾቼ ተግብረዋል” ሳምሶን አየለ – ስሑል ሽረ
” ይዘን የመጣነው ነገር በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነው። በሁለቱም 45 ደቂቃ ለመተግበር ያሰብነውን እቅድ ተጫዋቾቼ ተግብረዋል። ተጫዋቹቹን ላመሰግንም እፈልጋለው። የሜዳው አለመቸት እንዳለ ሆኖ እንቅስቃሴው ጥሩ ነበር። ቡድኑ ከባለፈው ጊዜያት እጅጉን የተሻለ ነው ከዚህም በኋላ ያሉብን ክፍተቶች ላይ የምንሰራ ይሆናል።”
የዳኛን ውሳኔ በፀጋ ያለመቀበል
” ትክክል ነው፤ ረዳቶቼ ወጣቶች ናቸው፤ ስሜትን የመቆጣጠር ችግር አለ። ወደውስጥም ይህን ገምግመን ያየናቸው ችግሮች ነበሩ። በቀጣይ እያስተካከልን እንሄዳለን። እናንተም እንዳላችሁት ይህ ዓይነቱ ድርጊት ስፖርታዊ ጨዋነት ያጓድላል። እነዚህን ወደፊት እነኚህን ችግሮች እየቀረፍን እንሄዳለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ