የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-0 ባህር ዳር ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ከተማን አስተናግዶ 3 -0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

👉 ” ሜዳችን ላይ የምናስቆጥራቸው ግቦች መበርከት ለቡድናችን ትልቅ ኃይል ነው” ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

ማሸነፋችን ትልቅ ነገር ነው። እስካሁን በሜዳችን ሦስት ጨዋታ አድርገናል፤ ዛሬ ግን እንደጠበኩት አላገኘውትም። በተላይ ባህር ዳር ከተማ የኳስ ቁጥጥራቸው ጥሩ ነበር፤ ጥሩ እቅስቃሴ ነበራቸው። የኛ እንደገባኝ ባለፈው 3-1 እየመራን በሰበታ የተቆጠሩብን ሁለት ጎሎች እና አቻ መጠናቀቁ እስካሁን በተጫዋቾቼ ስሜት ውስጥ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ይሄን ጨዋታ ለማሸነፍ ሙሉ ስሜታቸውን ይዘው ነው የገቡት። የሚቀጥለው ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ጋር እንደመሆኑ ይሄ ነጥብ አስፈላጊያችን ነው። በልጆቹ በኩል ያየሁት የግላዊ በራስ መተማመን እስካሁን ካደረግነው ያነሰ ነው። ቢሆንም ጨዋታው ግብ ለማስቆጠር ያለን ኃይል ትልቅ እንደሆነ ነው ያሳየን። አንድ ሰው ሦስት ሰው አይደለም። ከዛ በላይ ያሉት የማግባት ዕድል አላቸው። ትልቅ ጎናችን ይሄ ነው። ኳስ ጨዋታ ሁሌም አንድ አይነት ላይሆን ይችላል። ግን እስካሁን ሜዳችን ላይ የምናስቆጥራቸው ግቦች መስፋት ለቡድናችን ትልቅ ኃይል ነው። በተረፈ ባህርዳሮች ዛሬ ያደረጉትን ጨዋታ ሳላደንቅ አላልፍም።

የሰዒድ ሀሰን በመሀል ተከላካይነት መሰለፍ

በዓመቱ የምናደርገው 30 ጨዋታ ነው። ቡድኑ እንደ ቡድን በተወሰኑ ተጫዋቾች ክፍተት አይኖረውም። ያሬድ ባየህ ትልቁ ተጫዋቻችን ነው። ነገር ግን ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ባይኖርም አሸጋሽገን እየተጠቀምን ነው። ብዙም ክፍተት አላየሁም። ሰዒድ ሀሰን ቦታውን ሸፍኖ ጥሩ እየተጫወተ ነው። የሰዒድን ቦታ ታዳጊው ዓለምብርሀን ሸፍኖ እየተጫወተ ነው። ጥሩ በመጫወት ሌሎች ታዳጊዎችንም እያነቃቃ ነው በአጠቃላይ ያለው ነገር ጥሩ ነው። በጉዳት ያጣናቸው ሲመለሱ ይበልጥ እንጠናከራለን።



👉 “እነሱ ያገኛቸው የጎል ዕድሎችን መጠቀማቸው እና የሰራናቸው የመከላከል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል” ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከነማ

ስለ ጨዋታው

በመጀመሪያ ተጋጣሚያችን ጨዋታውን ስላሸነፈ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በመቀጠል በጨዋታ ላይ እነሱ ያገኟቸው የጎል ዕድሎችን መጠቀማቸው እና የሰራናቸው የመከላከል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል። በእርግጥ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ጎል ከተቆጠረብን በኋላ የተጋጣሚያችን ተጫዎቾች በመውደቅ ጨዋታውን ማቀዝቀዝ በመፈለጋቸው ወይም እንደ ታክቲክ በመያዛቸው በምንፈልገው አጨዋወት አጥቅተን ጎል ማግባት አልቻልንም። እንደዛም ሆኖ ግን ከመጀመርያው ጀምሮ ፋሲል በሜዳው ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለናል።

የሲሶኮ እና ሲዲቤ አለመኖር የፈጠረው ክፍተት የቆሙ ኳሶችን ከመጠቀም ችግር አንፃር

የቆሙ ኳሶች አጠቃቀማችን ዛሬ ጥሩ አልነበረም። እነዛ ተጫዎቾች አልነበሩም ብዬ ሜዳ ላይ የነበሩትን ተጫዎቾች ጥረት ማሳነስ አልፈልግም። ተጫዋቾቼ ሜዳ ላይ የሚችሉትን አድርገዋል። ወደዚህ የመጣነው ፋሲልን ለማሸነፍ ነው ፤ አልተሳካልንም። ስህተቶቻችን ላይ በተለይ በመከላከሉ ላይ ያጋጠሙን ስህተቶች ላይ ጠንክረን በመስራት ከዚህ መማር እንዳለብን ይሰማኛል።

ከሜዳ ውጪ ነጥብ የመያዝ ችግር

እንዳልኳችሁ ነው። ከሜዳ ውጪ ያለንን ድክመት ለመስበር ነው ወደዚህ ሜዳ የመጣነው። እንዳያችሁት ሜዳው ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል። ጨዋታውን ለማሸነፍ ፈልገን ነበር። ግን በማጥቃት ያገኙትን ዕድሎች በመጠቀም ከእኛ እነሱ የተሻሉ ስለነበሩ ጨዋታውን ማሸነፍ ችለዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ