ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ፈረሰኞቹ እና ምዓም አናብስትን የሚያገናኛው የስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በወጣ ገባ አቋም ውድድራቸው በማካሄድ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾቻቸው ከጉዳት መልስ ቢያገኙም ወደ ጥሩ የማሸነፍ መንገድ መምጣት ተስኗቸዋል። ጊዮርጊሶች ሰበታ ከተማን ካሸነፉ በኃላ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ በጅማ አባጅፋር ሽንፈት የገጠማቸው ሲሆን ከመሪዎቹ በነጥብ ላለመራቅ ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።

ከተለመደው የቡድኑ የመስመር አጨዋወት ወጣ ብለው መሀል ለመሐል በሚደረጉ የማጥቃት አጨዋወቶች ለመቅረብ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በነገው ጨዋታ ሳልሀዲን ስዒድን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። በዚህም ሳልሀዲን ስዒድ ወደ ቋሚ አሰላለፍ የሚመለስ ከሆነ ቡድኑ ሳልሀዲን ለመጨረሻ ግዜ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች እንደተከተለው አጨዋወት አጥቂው ላይ ያነጣጠረ የማጥቃት አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ይጠበቃል።

ፈረሰኞቹ ሳልሀዲን ስዒድ እና ሳልሀዲን በርጊቾ ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ለአለም ብርሀኑ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አቡበከር ሳኒ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

በተከታታይ ጨዋታዎች ወሳኝ ድሎች አስመዝግበው ወደ ጥሩ የማሸነፍ መንገድ የተመለሱት ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታም የሰመረ የማሸነፍ መንገዳቸው ለማስቀጠል ወደ ጨዋታው እንደሚገቡ ይጠበቃል።

በወሳኝ የአማካይ ተጫዋቾቻቸው መጎዳት ምክንያት በሁለቱ አጥቂዎች መሰረት ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት እና የመስመር ላይ ያደላ አጨዋወት ለመተግበር ጥረት በማድረግ የቆዩት መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ዮናስ ገረመው እና ዳንኤል ደምሱ ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ተከትሎ አቀራረባቸው ላይ ለውጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም የፈጠራ አቅም ማነስ ታይቶበት የነበረው ቡድኑ የማጥቃት አማራጮች ከማስፋቱም በተጨማሪ የአማኑኤል ገ\ሚካኤል ፣ ኦኪኪ ኦፎላቢ እና ያሬድ ከበደ ጥምረት ከግዜ ወደ ግዜ መሻሻሎች ማሳየቱ የማጥቃት አቅሙ አስፈሪ አድርጎታል። ቡድኑ በነገው ጨዋታም በተጠቀሰው ጥምረት ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዞ መግባቱ አይቀሬ ነው።

መቐለዎች በነገው ጨዋታ በረጅም ግዜ ጉዳት ላይ ያለው ሚካኤል ደስታ በጉዳት አያገኙም በአንፃሩ ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ዳንኤል ደምሱ ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው ይደርሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ዓብዱልከሪም መሐመድ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – አስቻለው ታመነ – ሄኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ሙሉአለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ

ቴቦ ዛጉዌ- ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንድ ኤድዋርድ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ዮናስ ገረመው – ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሱ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ