የኢትዮጵያ ሊግ ዋንጫ ፡ የታደለ መንገሻ ጎል አርባምንጭን ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲያሻግር ቡና በመለያ ምቶች አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሊግ ዋንጫ (የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ብቻ የሚሳተፉበት የጥሎ ማለፍ ውድድር) የመጀመርያ ዙር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ አርባምንጭ እና ኢትዮጵያ ቡናም ወደ ሩብ ፍፃሜው የሚያሻግራቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በ9፡00 ሀዋሳ ከተማን የገጠመው አርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸንፏል፡፡ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ ፣ የግብ ሙከራዎች ያልነበሩበት እና ምንም የፉክክር መንፈስ የታየበት ይህ ጨዋታ በስፍራው የተገኘውን ተመልካች አበሳጭቷል፡፡ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ጥቂት የግብ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት አርባምንጮች ዘንድሮ ቡድኑን በተቀላቀለው ታደለ መንገሻ ወሳኝ ግብ አማካኝነት በአምናው የፍጻሜ ተፋላሚ ላይ የ1-0 ድል አስመዝግበዋል፡፡ በጨዋታው ላይ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ኳስ ሲይዙ ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ተቃውሞ ሲሰማባቸው ተስተውሏል፡፡

በ11፡30 ኢትዮጵያ ቡና በደጋፊዎቹ ታጅቦ ሀዲያ ሆሳዕናን በመለያ ምቶች አሸንፏል፡፡ ጨዋታው በ90 ደቂቃዎች ግብ ያልተቆጠረበት ሲሆን የመጀመርያው አጋማሽ ልክ እንደ አርባምንጭ እና ሀዋሳ ጨዋታ ሁሉ ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ ሙከራዎች ቢያደርግም ኢላማቸውን የሳቱ እና የግቡን አግዳሚ የመለሳቸውን ጨምሮ ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ የሀድያ ሆሳዕና ግብ እንዳይደፈር ወሳኙን ሚና ተጫውቷል፡፡

90 ደቂው ካለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የፍፁም ቅጣት ምቶች ኢትዮጵ ቡና 4-2 አሸንፏል፡፡ አየለ ተስፋዬ እና አምበሉ አድናን ቃሲም ከሃድያ ያመከኑ ሲሆን ከቡና የተመቱት በሙሉ ተቆጥረዋል፡፡ ዮሴፍ ዳሙዬ ያስቆጠራት የመጨረሻ የመለያ ምት በተለምዶ ‹‹ፓኔንካ›› ተብሎ በሚጠራው የፍፁም ቅጣት ምት አመታት ነው፡፡

የ1ኛ ዙር ቀጣይ ጨዋታዎች ነገ ሲካሄዱ ከዛሬ ወደ ነገ የተላለፈው የአዳማ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ8፡00 ሲደረግ አበበ ቢቂላ ላይ በ8፡00 ሲዳማ ቡና ከ ዳሽን ቢራ ፣ በ10፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ፡፡

IMG_1809

ያጋሩ