የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀመረ

በካናዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላለበት የማጣርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀምሯል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ህይወት አረፋይኔ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በጥር ወር የመጀመርያ ሳምንት ከቡሩንዲ ጋር የመጀመርያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ለዚህም እንዲረዳቸው በቅርቡም ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በትናትናው ዕለት አመሻሽ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመርያ ልምምዳቸውን ሠርተዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በሙሉ በልምምዱ ወቅት የተሳተፉ ሲሆን ከጨዋታው አስቀድሞ ባሉት ቀሪ ቀናቶች ልምምዳቸውን እየሰሩ ይቆዩና ሦስት ተጫዋቾችን በማስቀረት 20 ተጫዋቾችን በመያዝ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ ለማድረግ ወደ ቡሩንዲ የሚያቀኑ ይሆናል።

አጠቃላይ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እና የቡድኑ አንበል በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ እንደሆነ ሰምተናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ