ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ምዓም አናብስትን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አአ ስታዲየም ላይ መቐለ 70 እንደርታን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ካስተናገዱበት የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ምንተስኖት አዳነ እና ያብስራ ተስፋዬን በአስቻለው ታመነ እና ሳልሃዲን ሰዒድ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ ተጋባዦቹ መቐለዎች ደግሞ ከባለፈው ሳምንት የመጀመርያ 11 ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል።

ሳቢ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመርያ 45 ሁለቱም ቡድኖች መሃል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጫውተዋል። በአንፃራዊነት ከመቐለ በተሻለ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታ ብልጫ ወስደው ተንቀሳቅሰዋል። ሳልሃዲን ሰዒድ የመቐለ የግብ ክልል አካባቢ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል በመታው ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ተስተናግዷል። ከደቂቃ በኋላም ጊዮርጊሶች ከመዓዘን መት ሌላ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ በደስታ አማካኝነት ፈጥረው መክኖበታል።

በአንፃራዊነት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ጨዋታቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት መቐለዎች የጠራ የግብ ማግባታ አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸው ታይቷል። በተቃራኒው በሚገርም የደጋፊ ድባብ ታጅበት ጨዋታቸውን የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ ሄኖክ አዱኛ በ24ኛው ደቂቃ ከመስመር ሰብሮ በመግባት በሞከረው ጥሩ ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል። ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ የጨዋታ ዘይቤን መከተል የጀመሩት መቐለዎች በ28ኛው ደቂቃ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል ደርሰው ታይተዋል። በዚህ ደቂቃ አማኑኤል ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ሮጦ በመውጣት ወደ ግብ ሊሞክር ሲል በጥሩ ሰዓት ግብ ክልሉን ለቆ የወጣው ባህሩ ኳሱን አፅድቶበታል።

በሦስት አጥቂዎች የፊት መስመራቸውን እየመሩ የነበረው ጊዮርጊሶች ሳልሃዲን ለአቤል አመቻችቶ አቤል በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ በመታው ኳስ የመቐለን የግብ ክልል መፈተሻቸውን ቀጥለዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ቡድኑ በ36ኛው ደቂቃ ጋዲሳ በሞከረው ጥብቅ ኳስ ለመሪነት ተቃርበው ነበር።
ከመቐለ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው የሰርጂዮ ተጫዋቾች ጥቃት መሰንዘራቸውን አላቆሙም። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ሳልሃዲን ከርቀት አክርሮ በመታው እና ጌታነህ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ በግምባሩ በመግጨት ወደ ግብ በላከው አጋጣሚዎች የግቡን መረብ ለማግኘት ጥረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆም በጭማሪ ሰዓት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሳልሃዲን ተጨማሪ ሙከራ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ሳላዲን ወደ ግብ የመታው ኳስ መረብ ላይ ሳያርፍ አጋማሹ ተጠናቋል።

ኳስ እና መረብን ማገናኘት ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተጠናክረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። አጋማቹ በተጀመረ 3 ደቂቃዎች ውስጥም ሦስት ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረው ወደ መቐለ የግብ ክልል ደርሰዋል። ገና እደተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ አቤል ሥዩም ተስፋዬን አታሎ ወደግብ በመታው እንዲሁም ከደቂቃዎች በኋላ ጌታነህ እና ሃይደር ከሳጥን ውጪ አክርረው በመቱት ኳስ ጫናዎችን ፈጥረዋል። ይህ ብቻ አልበቃ ያላቸው ባለሜዳዎቹ የጨዋታ ብልጫቸውን በጎል ለማጀብ በ53ኛው ደቂቃ ጥሩ አጋጣሚ በጌታነህ አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል።
ተጋባዦቹ መቐለዎች በበኩላቸው ከመጀመሪያው አጋማሽ አጨዋወታቸው ሻል ብለው ለመቅረብ ሞክረዋል። በዚህም በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ሲጫወት የነበረው ቡድኑ ኳስን ለመቆጣጠር በማለም ወደ መሃል ሜዳ ለመጠጋት ጥሯል። ይህ የተጋጣሚያቸው ውሳኔ የጠቀማቸው የሚመስለው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ58ኛው ደቂቃ የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃ በጥሩ የኳስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ አንጋፋው አጥቂ ሳልሃዲን ሰዒድ ከፍሊፕ ኦቮኖ ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል። 

በዚህ ጎል ተገትተው ወደ መቐለ የግብ ክልል መጓዝ ያላቆሙት ጊዮርጊሶች በ63 እና 64ኛው ደቂቃ አቤል እንዲሁን ጌታነህ በሞከሩት ጥሩ ሙከራ መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረዋል።

ኦኪኪ አፎላቢን አላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች በመላክ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያሰቡት መቐለዎች ልፋታቸው ገደል የሚከት አጋጣሚ በ76ኛው ደቂቃ ተፈጥሯል። በ60ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ (ቢጫ) ከእለቱ ዳኛ የተመለከተው አንተነህ ገ/ክርስቶስ ከ16 ደቂቃዎች በኋላ ዳግም ጥፋት በመስራቱ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። እቅዳቸውን በድጋሚ እንዲከልሱ እድል የሰጣቸው ይህ ክስተት ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በፈተና እንዲያከናውኑት አድርጓቸል።

በዚህ አጋማሽ የሚፈልጉትን ያገኙት ባለሜዳዎቹ በበኩላቸው ኳስን በትዕግስት በመቀባበል ተጨማሪ ግቦችን ለማምረት ተንቀሳቅሰዋል። ሙሉ 90 ደቂቃው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀረው አቤል የቡድኑን መሪነት ከፍ አድርጓል። በዚህ ደቂቃ ከጨዋታ ውጪ እንዳይሆን በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አቤል ከተከላካዮች መሃል በመገኘት ያገኘውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል።

ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቧቸው ታታሪ ተጨዋቾች ታግዘው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት ሲሞክሩ የነበሩት ምዓም አናብስቶች ሙሉ 90 ደቂቃዉ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት አሸናፊ ሃፍቱ ባስቆጠረው ኳስ መሪነቱን አጥበውታል። እጅግ የዘገየችው የአሸናፊ ጎል ቡድኑን መታደግ ሳትችል ጨዋታው ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ 13ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 9 በማድረግ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጨዋታውን ቢያሸንፍ የሊጉ መሪ መሆን ይችል የነበረው መቐለ 70 እንደርታ ባለበት 3ኛ ደረጃ ላይ በ10 ነጥብ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ