የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 መቐለ 70 እንደርታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቐለ 70 እንደርታ ካደረጉት የ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለብዙሃን መገናኛዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

👉”በእኛ እምነት ለሌላቸው እና ቡድኑ ጎል አያገባም ለሚሉ መልስ ሰጥተናል።” ሰርዳን ዝቮጂኖቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

በቅድሚያ ተጨዋቾቼን ማድነቅ እፈልጋለሁ። በሙሉ 90 ደቂቃዉ ሲታገሉ ነበር። በቀጣይ ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ልዩ እና የሚገርም ድጋፍ ነበር ሲቸሩን የነበረው። ወደ ጨዋታው ስመለስ ጥሩ ጨዋታ ነበር። በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። በእኛ እምነት ለሌላቸው እና ቡድኑ ጎል አያገባም ለሚሉ መልስ ሰጥተናል። ከዚህ በፊትም እንቅስቃሴ ነው ጎል ከዛ ይመጣል ብዬ ተናግሬ ነበር። አሁን የምናስበው ለረቡዕ ጨዋታችን ነው። በጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ነው። ግን ከዚህ በኋላ ስለ ቀጣይ ጨዋታችን ማሰብ አለብን። እኔ በግሌ አሁን አዕምሮዬ ውስጥ ያለው ቀጣዩ የሀዋሳ ጨዋታ ነው።

ስለ ቀይ ካርዱ

ቀይ ካርዱን እኔ አላየሁትም። ግን ዳኛውን ስለማምነው ችግር የለውም። አይደለም ለቀይ ካርዱ ከእሱ በፊት በመጀመሪያው አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጠን ሲገባ ለከለከለንም አምኜዋለው። ስለዚህ ይህ የዳኛው ውሳኔ ነው። በግሌ ስለ ዳኛው ውሳኔ ምንም ማለት አልፈልግም።

👉”የተወሰኑ ችግሮች ቢኖሩብንም የራሳችን የብስለት አለመኖር ችግር ዋጋ አስከፍሎናል።” ገብረመድህን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ መልኩ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። ከእረፍት በኋላ ግን ለውጦች ነበሩ። የተወሰነ ችግሮች ቢኖሩብንም የራሳችን የብስለት አለመኖር ችግር ዋጋ አስከፍሎናል። በአጠቃላይ በግልም ስህተቶችን ስንሰራ ነበር። እነሱ ግን ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲፈጥሩብን ነበር። እነሱ ብቻ ሳይሆን ዳኛውም ከፍተኛ የሃይል ጨዋታን በመፍቀድ ጫና ፈጥሮብናል። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ደግሞ ተጨዋቾቼ ተረጋግተው እንዳይጫወቱ አድርጓቸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጥሩ ቡድን ነው። እኛ በስነ ልቦናም ረገድ የነበረንን የበላይነት መጠቀም አልቻልንም።

ስለፈጠሯቸው የግብ እድሎች አናሳነት

ልክ ነው። በቂ የሚባል የግብ እድሎች በእኛ በኩል አልተፈጠሩም። የመጀመሪያ አላማችን ኳስን ተቆጣጥሮ በጋራ የመሄድ የሚል ነበር። ይህንን ደግሞ ተጨዋቾቼ ማድረግ አልቻሉም። በእረፍት ሰዓትም ለተጨዋቾቼ ሙከራዎችን እንዳላደረግን ነግሬያቸው ወደ ሜዳ ገብተናል። ነገር ግን ገና በጊዜ እነሱ አግብተውብን የጨዋታው መልክ ተቀይሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ