ከፍተኛ ሊግ ሀ | ለገጣፎ መሪነቱን ሲረከብ ደሴ ከተማ እና ደደቢት አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት ተካሂደዋል። ለገጣፎ ወደ አንደኝነቱ ሲመለስ ደደቢት ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል። ደሴ ከተማም ወደ ድል ተመልሷል።

በሳምንቱ ከተጠበቁ ጠንካራ ጨዋታዎች መካከል የነበረው የደሴ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ደሴ ላይ ተከናውኖ ባለሜዳው 1-0 አሸንፏል። የጦሳ ፈርጦቹን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል በግምባሩ በመግጨት ያስቆጠረው በ89ኛው ደቂቃ ላይ በድሩ ኑርሁሴን ነው።

ለገጣፎ ለገዳዲ በሜዳው ወልዲያን አስተናግዶ 3-0 በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አናት ከፍ ብሏል። ቡድቹ ያለ ጎል ወደ ዕረፍት ያመሩ ሲሆን ልደቱ ለማ 48ኛው እና አብዲሳ ጀማል በ51ኛውደቂቃ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች መምራት ችለዋል። የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ልደቱ 82ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ፣ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው ተጠናቋል።

ወደ ደብረብርሃን ያመራው ደደቢት የከፍተኛ ሊግ የመጀመርያ ድሉን አሳክቷል። ከእረፍት መልስ አፍቅሮት ሰለሞን ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ለደደቢት ሦስት ነጥቦችን አስገኝታለች።

አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ከገላን ከተማ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። አክሱሞች ዘካርያስ ፍቅሬ በ33ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም ከሁለት ደቂቃ በኋላ ብሩክ እንዳለ ለገላኖች ግብ አስቆጥሮ አቻ ማድረግ ችሏል።

ሶሎዳ ዓድዋ እና ወሎ ኮምቦልቻ እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ያለ ግብ የተጠናቀቁ መርሐ ግብሮች ናቸው።

የደረጃ ሠንጠረዥ

የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ