ከፍተኛ ሊግ ለ | መከላከያ እና ሀምበሪቾ ወደ ሠንጠረዡ አናት ሲጠጉ ሶዶ እና ጨንቻ አሸንፈዋል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ መከላከያ፣ ሀምበሪቾ፣ ወላይታ ሶዶ እና ጋሞ ጨንቻ ድል አስመዝግበዋል።

መከላከያ በሜዳው በሜዳው ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች በተለይ አጥቂዎቻቸው ፍቃዱ ዓለሙ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ወጣቱ መሐመድ አበራ ከኳስም ከኳስ ውጭ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአባ ቡናዎች ተከላካዮች ፈተኝ ነበር። በተደጋጋሚ ወደ አባቡና ወደ ጎል የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በ15ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ ታፈሰ በጥሩ ሁኔታ በተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ምንይሉ ወንድሙ በግሩም አጨራረስ የመከላከያን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል።

ከግቡ ቆጠር በኃላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መከላከያዎች 26ኛው ደቂቃ በዕለቱ ከመስመር እየተነሳ በማጥቃት ሽግግሩ ላይ ከፍተኛ አስተዋፆኦ የነበረው ተከላካይ ከሽመልስ ተገኝ ከመስመር የተሻገረለት ወጣቱ አጥቂ መሐመድ አበራ በግንባሩ በመግጨት የመከላከያን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

መከላከያ ጎሉን ካስቆጠረ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ከቅጣት ምት ወደ መከላከያ የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ በግብጠባቂው አቤል ማሞ እና በተከላካዮች አለመናበብ ምክንያት የተገኘውን ኳስ የአባ ቡና አንበል ዳዊት ታደሰ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

አባቡናዎች በወጣት የተገነባ ጥሩ ቡድን ቢሆንም በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የነበራቸው ቅንጅት አንድ ጎል ካስቆጠሩበት የጎል አጋጣሚ ውጭ እምብዛም ወደ ጎል የደረሱበት አጋጣሚ አለመኖሩ ጨዋታውን አክብዶባቸዋል።

ወደ እረፍት መዳረሻ 42ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሽመልስ ተገኝ ከመስመር ያሻገረውን ከረጅም ጉዳት መልስ ወደ ሜዳ ተመልሶ እየተጫወተ የሚገኘው ምንይሉ ወንድሙ ወደ ምርጥ አቋሙ መመለሱን ያሳየበትን ግሩም የግንባር ጎል በማስቆጠር የመከላከያን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ያለቀ በሚመስል ሁኔታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዞ ቀጥሎ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እንደገባ በሜዳ ውስጥ አምስት ደቂቃ የቆየው የቀድሞ የሙገር እና ጅማ አባ ጅፋር አማካይ አብዱልከሪም አባፎጊ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶ ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾን ከ ሀላባ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከወልቂጤ ቡድኑን የተቀላቀለው ቢንያም ጌታቸው በ65ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾን የአሸናፊነት ግብ አስቆጥሯል።

ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከአዲስ አበባ ያደረጉት ጨዋታ በ46ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ፋሲካ ባስቆጥራት ብቸኛ ግብ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ጨንቻ ላይ ኢኮሥኮን ያስተናገደው ጋሞ ጨንቻ 2-1 አሸንፏል። በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ገና ከጅምሩ ጎሎች አስተናግዷል። በሁለተኛው ደቂቃ ዘላለም አክርሮ ወደግብ የላካትን ኳስ የኢኮሥኮ ግብ ጠባቂ መትፋቱን ተከትሎ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ማቴዎስ ኤልያስ ወደ ግብነት ቀይሮ ባለሜዳዎች 1-0 መምራት የቻሉ ሲሆን ይህ መሪነታቸው ግን መቀጠል የቻለው ለ3 ደቂቃ ብቻ ነበር።  የጋሞ ጨንቻ ተከላካዮችን አለመናበብ ተከትሎ በግምት ከ25 ሜትር አከባቢ ዳግማዊ ዓባይ ወደ ግብ የመታት ኳስ መረብ ላይ አርፋ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በሁዋል ቅርፅ አልባ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርካታ የግብ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን በ73ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ታደለ በቀለ ያሻገራት ኳስ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በበርካታ ተጫዋቾች ተጨራርፋ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ለገሰ ዳዊት ስትደርስ በተገቢው ሁኔታ ተጠቅሞበት ባለሜዳዎቹወደ መሪነት እንዲመለሱ አድርጓል።

ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ከሻሸመኔ ባደረጉት ጨዋታ የከፍተኛ ሊግ ፈጣኑ ግብ ተቆጥሯል። አድናን ረሻድ ከአንድ ደቂቃ ሳይሞላ ጎል በማስቆጠር ካፋን ቀዳሚ ሲያደርግ ለሻሸመኔዎች ኤርምያስ ዳንኤል በ14ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ በአቻ 1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ሚዛን አማን ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከ ነቀምት ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

የደረጃ ሠንጠረዥ

የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ

 


© ሶከር ኢትዮጵያ