ከፍተኛ ሊግ ሐ| አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን ሲያጠናክር መድን፣ የካ፣ ወራቤ እና ቡታጅራ አሸንፈዋል

ምድብ ሐ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲከናወኑ አርባምንጭ መሪነቱን አስፍቷል። ስልጤ ወራቤ እና ቡታጅራ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ኢትዮጵያ መድን እና የካ ክ/ከተማ የዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን አሳክተዋል።

አርባምንጭ ከተማ 2-1 ነገሌ አርሲ

/ፋሪስ ንጉሴ/

መሪው አርባምንጭ ከተማ አርሲ ነጌሌን የገጠመበት የዛሬው መርሃ ግብር እንደ ሁልጊዜው በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጀመረ ሲሆን አዞዎቹ በተጋጣሚያቸው ላይ የኳስ ብልጫ ከመውሰድ ይልቅ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። የጨዋታው 5ኛ ደቂቃ ላይም አብነት ተሾመ ለኤደም ኮድዞ በግንባሩ አመቻችቶ አቀብሎ ኤደም በሚገባ ከተቆጣጣረ በኋላ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ወዲ ውጭ የመታው የሚያስቆጭ ሙከራ ነበር።

28ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የኳስ ቅብብል
ምንተስኖት አበራ ለአርባምንጭ ከተማዎች ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችልም በተከላካዮች ከሽፎበታል። በዝህች ኳስ ላይም ባለሜዳዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር ሲሉም ለመሀል ዳኛው ቅሬታ አሰምተዋል። 31ኛ ደቂቃ ላይ ወርቅይታደስ አበበ ከመስመር ያሻገረውን ኤዶም በግንባሩ ገጭቶ ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

33ኛ ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኝ ከምንተስኖት አበራ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል ሞክሮ በግብ ጠበቂው ሲመልስበት እንግዳዎቹ በአላዛር ዘነቡ ጥሩ የማግባት ዕድል መፍጠር ቢችሉም በአርባምንጭ ተከላካዮች ተመልሶበታል። የመጀመርያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከተማ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ባለሜዳዎቹ 54ኛ ደቂቃ ላይ በኤደም ኮድዞ ያለቀለት ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። እንግዳዎቹም ጫና ፈጥረው በመጫወት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። 64ኛ ደቂቃ ላይ አላዛር ዝናቡ የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘው ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ እግዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አርባምንጭ ከተማዎች በተደጋጋሚ የእንግዳውን ብድን ተከላካዮች ሲፈትኑ ቆይተዋል። በተደጋጋሚ በኤደም ኮድዞ እና በአሸናፊ ተገኑ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተለይ እሱባለው ፍቅሬን ፍቃዱ መኮንን እና አቦነ ገለቱን በተከታታይ ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ በጨዋታው ለይ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ነገር ግን እንግዳዎቹ ነጌሌ አርሲዎች በመልሶ ማጥቃት ባለሜዳዎቹን አልፎ አልፎም መፈተናቸው አልቀረም። በተለይ በአላዛር ዝናቡ የሚፈጥሩት ዕድሎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

የጨዋታው ማብቃያ ላይ አርባምንጭ ከተማዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች እና በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድሎች ለመፍጠር በተደጋጋሚ የእንግዳዎቹን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲደረሱ ቆይተዋል። በጨዋታው ልዩ እንቅስቃሴ ያደረገው ፍቃዱ መኮንን 92ኛ ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ሁለት ተጫዋቾችን አታሎ ያሻማው ኳስ በአርሲ ነጌሌው ተከላካይ በእጅ በመነካቱ የመሀል ዳኛው የፍፁም ቅጣት ለአርባምንጭ ከተማ ሰጥተዋል። ኤደም ኮድዞም አጋጣሚውን ወደ ጎል ቀይሮ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2ለ1አሸናፊነት ተጠናቋል።

ደቡብ ፖሊስ 0-1 ስልጤ ወራቤ
/ቴዎድሮስ ታከለ/

ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ስልጤ ወራቤን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል። ማራኪ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቢጫ ለባሾቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ ስኬታማ ግን አልነበረም። በአንፃሩ ስልጤ ወራቤዎች የደቡብ ፖሊስን የቅብብል እና የአደረጃጀት ስህተት በመጠቀም በሚያገኙት አጋጣሚ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል። በ26ኛው ደቂቃ ላይም የማሸነፊያዋን ግብ አግኝተዋል፡፡ ከቅብብል ስህተት አጥቂው ተመስገን ዱባ ያገኛትን ኳስ ለከድር ታረቀኝ አመቻችቶለት ወደ ግብነት ተለውጣለች።

ከግቧ በኃላ ወደ እንቅስቃሴ በቶሎ ለመግባት የዳከሩት ቢጫ ለባሾቹ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ስልጤ ወራቤዎች 41ኛው ደቂቃ አምበሉ ሮባ ዱካሞ ከግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ላይ የሰቀላት አጋጣሚ ምናልባት የወራቤን ልዩነት የምታሰፋ ነበረች፡፡

ብዙም ሙከራ እና የተለዩ እንቅስቃሴዎች ባልተመከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ ስልጤ ወራቤዎች አስጠብቆ ለመውጣት በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ ሲወድቁ የነበረ ሲሆን በሒደቱም በርከት ያሉ ቢጫ ካርዶች ተመዞባቸዋል። ከዚህ ውጪ አጥቂው ተመስገን ገብረፃድቅ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ ገብቶ በስልጤ ወራቤ ተከላካይ ጉዳት የገጠመው ሲሆን በዚህ ክስተት ወቅት በተሰራው አደገኛ ጥፋት የእለቱ ዳኛ ካርድ አለማሳየታቸው ከደጋፊው ተቃውሞን አስተናግዷል። አሰልቺ የነበረው ሁለተኛ አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት በስልጤ ወራቤ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሌሎች ጨዋታዎች

/አምሐ ተስፋዬ/

ኦሜድላ ሜዳ ላይ አዲስ አዳጊው ቂርቆስ ቅዳሜ ዕለት ቡታጅራ ከተማን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል። እንግዳው ቡድን አብዱልከሪም ቃሲም በ68ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ነበር አሸንፎ መውጣት የቻለው።

ዛሬ ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ7:00 የካ ክፍለ ከተማን ከኮልፌ ያገናኘው ጨዋታ በየካ ክፍለ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አሸናፊ ምትኩ በ34 ኛው እንዲሁም ሙሴ ተክለወይኒ በ65ኛው ደቂቃ ላይ የየካን ግቦች ሲያስቆጥሩ ለኮልፌ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሙሉጌታ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ከ ሺንሺቾ ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል። ባለሜዳዎቹ ያሬድ ሀብታሙ በ34ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ እየመሩ ወደ ዕረፍት ቢያመሩም ከእረፍት መልስ ሀብታሙ ከበደ ሺንሺቾን ነጥብ ያጋራች ጎል አስቆጥሯል።

ኢትዮጽያ መድን በሜዳው ጌዲኦ ዲላን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። በ65ኛው ደቂቃ ላይ አንጋፋው ብርሃኑ ቦጋለ የመድንን የዓመቱ የመጀመርያ ድል ያስገኘች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

የደረጃ ሠንጠረዥ



የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ



© ሶከር ኢትዮጵያ