የፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ጎል

– በአምስተኛ ሳምንት በአጠቃላይ 15 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች በ6 ያነሰ ነው።

– በዚህ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርባቸው ተጠናቀዋል። የዘንድሮው ሊግ ከጀመረ ወዲህም ከአንደኛው ሳምንት ጋር በጋራ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ከ16 ቡድኖች መካከልም 9 ቡድኖች ጎል ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። (ይህም ከፍተኛው ነው)

– በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት 15 ጎሎች በ14 የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። አንድ ጎል (የባህር ዳሩ ስንታየሁ መንግስቱ) በራስ ላይ የተቆጠረ ነው።

– ጎል ካስቆጠሩ 14 ተጫዋቾች መካከል 6 ጎሎች በመስመር፣ 6 ጎሎች (በራስ ላይ የተቆጠረውን ጨምሮ) በመሐል አጥቂዎች፣ 2 ጎሎች በአማካይ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል።

– አቡበከር ናስር ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግብ ቀሪዎቹ 13 ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከ15 ጎሎች መካከል 13 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ እና ከተሻሙ ኳሶች (ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምት) ሲቆጠሩ ቀሪዎቹ 2 ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው።

– ከዚህ ሳምንት 15 ጎሎች መካከል 3ቱ በግንባር ተገጭ ተመትተው የተቆጠሩ ናቸው። ሌሎቹ (12) ደግሞ በእግር የተቆጠሩ ናቸው።

– ለተቆጠሩ ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል ረገድ 11 ተጫዋቾች ተሳትፈዋል። ቀሪዎቹ በቆሙ ኳሶች (3) እና ከሙከራ ሲመለሱ (1) የተቆጠሩ ናቸው።

– ከ15 ጎሎች መካከል 14 ጎሎች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 1 ጎል ብቻ ከሳጥን ውጪ ተመትታ ተቆጥራለች።

ካርዶች

– አንድ ረዳት አሰልጣኝን ጨምሮ 33 ቢጫ እና አንድ ቀይ (ሁለተኛ ቢጫ) ካርዶች የተመዘዙት ይህ ሳምንት ከአራተኛው (37) እና ሁለተኛው ሳምንት (35) ቀጥሎ ሦስተኛው ነው።

– በወልቂጤ ከተማ (1 ቢጫ) እና ስሑል ሽረ (5 ቢጫ) እንዲሁም በሲዳማ ቡና (0) እና ድሬዳዋ ከተማ (6) መካከል የተደረጉት ጨዋታዎች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባቸው ሲሆን የሰበታ ከተማ (0) እና ወላይታ ድቻ (2) ዝቅተኛ ቢጫ ካርድ የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል።

በዚህ ሳምንት..

– አዳማ ከተማ ለአራተኛ ተከታታይ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።

– ድሬዳዋ ከተማ የዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን አስመዝግቧል።

– ሀዲያ ሆሳዕና ብቸኛው ድል ያላሸየሳካ ቡድን መሆኑን ቀጥሎበታል።

– ፋሲል ከነማ በሁሉም ውድድሮች በሜዳው ለተከታታይ ዘጠነኛ ጊዜ ተጋጣሚዎቹን አሸንፏል።

– ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው በሁለት ጨዋታ ብቻ ዘጠኝ ጎሎች ተጋጣሚዎቹ ላይ አዝንቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ