የሴቶች ከፍተኛ ሊግ (ሁለተኛ ዲቪዚዮን) ሁለተኛ ሳምንት አንድ ቀሪ ጨዋታ በንግድ ባንክ ሜዳ የክፍለ ከተማ ደርቢ ልደታን ከቦሌ አገናኝቶ ቦሌዎች በህዳት ካሡ ሐት-ትሪክ 3–0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ኳሱን መስረተው እና ተቆጣጥረው በመጫወት ልደታዎች የተሻሉ በሆኑበት የመጀመርያው አጋማሽ በሁለት አጋጣሚ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ መቅረታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። 26ኛው ደቂቃ የቦሌዎች ተከላካይ ኳስ ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት አጋጣሚ የልደታዋ አጥቂ የዘርሀረግ ተካልኝ በፍጥነት ገብታ የግብጠባቂዋ አዛለሽን አቋቋም ተመልክታ ኳስን ከግብጠባቂዋ አናት በላይ መታው ወደ ውጭ የወጣው፣ በተመሳሳይ መንገድ 41ኛው ደቂቃ እራሷ የዘርሀረግ ተካልኝ ከግብጠባቂዋ አናት ላይ ኳሱን አሳልፋው ገባ ሲባል ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣው ልደታዎችን መሪ ማድረግ የሚችሉ የሚያስቆጩ የጎል እድሎች ነበሩ።
የልደታን የጨዋታ እንቅስቃሴን በማቋረጥ የተመሰረተው የቦሌዎች አጨዋወት ሳይጠበቁ በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዝሯቸው አስደንጋጭ እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ ነበር። ይህም ተሳክቶላቸው በ44ኛው ደቂቃ የልደታ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅማ ህደት ካሱ በግራ እግሯ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ባስቆጠረችው ግሩም ጎል ቦሌዎችን ቀዳሚ ሆነዋል።
የልደታው አሰልጣኝ ዮናስ ውጤቱን ለመቀየር በወሰዱት ውሳኔ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ በአንዴ አምስት ተጫዎቾችን ቅያሪ በማድረግ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ተቀይረው የገቡት እየሩሳሌም ወንድሙና ፍሬህይወት በድሉ በተለያዩ ደቂቃዎች ያገኙትን አጋጣሚዎች አለመጠቀም የነበራቸውን ወደ ጨዋታው የመመለስ እድል አጨልሞታል።
ቡድኑን በተረጋጋ ሁኔታ ኳሶችን በማደራጀት ትልቁን ሚና ስትወጣ የነበረው የቦሌዎቹ አንበል ምስጋና ግርማ መሐል ሜዳ ላይ ያስጀመረችው ኳስ የልደታ ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ህዳት ካሱ በሚገርም ፍጥነትና አጨራረስ 64ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል ቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋዋለች።
ልደታዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በልጫ በውሰድ የጎል አጋጣሚዎችን አለመጠቀም ክፍተት በታየበት እና ያገኙትን የጎል አጋጣሚ ከአንድ አንድ የሚጠቀሙት ቦሌዎች በ74ኛው ደቂቃ በዕለቱ በአጨራረሷ ብቃቷ በጨዋታው ልዮነት የፈጠረችው ህዳት ካሱ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች።
በመጨረሻም ልደታዎች ተስፋ በመቁረጥ እንቅስቃሴያቸው እየወረደ ሲመጣ በአንፃሩ ቦሌዎች ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት በጠንካራ መከላከል ጨዋታውን ተቆጣጥረው 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያውን ሦስት ነጥብ አሳክተው ደረጃቸውን አሻሽለዋል።
የሁለተኛ ሳምንት ውጤቶች
ፋሲል ከነማ 0-1 ሻሸመኔ ከተማ
ቂርቆስ ክ/ከተማ 2-2 ጥሩነሽ ዲባባ
ባህር ዳር ከተማ 0-1 ንፋስ ስልክ
ልደታ 0-3 ቦሌ
ለገጣፎ ከ አካዳሚ (ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል)
© ሶከር ኢትዮጵያ