በነገው ዕለት ስሑል ሽረ እና ሰበታ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ የተንሸራተቱት ስሑል ሽረዎች በጥቂት ነጥቦች ከሚበልጧቸው ክለቦች ላለመራቅ እና ከተከታታይ አቻ ውጤቶች ለመውጣት የነገው ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል።
ሽረዎች በቡድኑ ውስጥ የነበረው የመከላከል ችግር በተወሰነ መልኩ የፈቱትና ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ የተከላካይ ክፍል የገነቡ ሲሆን ከባለፉት ተጋጣሚዎቻቸው አንፃር ሲታይ የተሻለ የአጥቂ ክፍል ያለው ቡድን እንደ መግጠማቸው የኋላ ክፍላቸው ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከሊጉ ጅማሬ አንስቶ ተመሳሳይ የመስመር አጨዋወት እየተከተሉ የሚገኙት ሽረዎች ነገም ከተለመደው አጨዋወት ወጣ ያለ አቀራረብ ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ባለፉት አራት ጨዋታዎች በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው የአጥቂ ክፍላቸው በነገው ጨዋታ ወደ ግብ ማስቆጠር እንዲመለስ የተወሰነ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።
ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ባለፉት ጨዋታዎች እንደ ተጋጣሚያቸው አቀራረብ የሚለዋወጥ አጨዋወት ይዘው የቀረቡት እና ቀስ በቀስ ወደ አሸናፊነት መንገድ የተመለስሱት ሰበታዎች ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታውን በማሸነፍ ጥሩ ጉዟቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን ያሸነፉት አዲስ አዳጊዎቹ በነገው ጨዋታ የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ይቸገራሉ ተብሎ ባይጠበቅም በተጋጣሚያቸው የመስመር አጨዋወት መፈተናቸው አይቀሬ ነው። ከወላይታ ድቻ ጋር በነበረው ጨዋታ የአማካይ ጥምረታቸው ላይ ለውጥ አድርገው የገቡት ሰበታዎች በነገው ጨዋታ ባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች እንደተከተሉት አጥቂዎቹን መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ አጨዋወት እና የመስመር አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሂደት መሻሻሎች እያሳዩበት ያሉ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ምርጫቸው አድርገው የሚገቡበት ዕድልም የሰፋ ነው።
ሰበታዎች በነገው ጨዋታ በረጅም ጊዜ ጉዳት ያለው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ፣ አስቻለው ግርማ እና ባኑ ዲያዋራን በጉዳት አያሰልፉም።
እርስ በርስ ግንኙነት
– የነገው ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ግንኙነት ሲሆን በከፍተኛ ሊግ በአንድ ምድብ ከተጫወቱበት 2010 በኋላም ለመጀመርያ ጊዜ ይጫወታሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ምንተስኖት አሎ
ዓብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ
ነፃነት ገብረመድህን – ሀብታሙ ሽዋለም
ዲድየ ሌብሪ – ያስር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ.
ብሩክ ሐድሽ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል አጃይ
ጌቱ ኃይለማርያም – አዲስ ተስፋዬ – ወንድይፍራው ጌታሁን – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ታደለ መንገሻ
ሲይላ ዓሊ ባድራ – ፍፁም ገብረማርያም – በኃይሉ አሰፋ
© ሶከር ኢትዮጵያ