ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና

ነገ ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች መካከል የሆነው የሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
በአዲሱ የውድድር ዓመት ማሸነፍ ያልቻለው ብቸኛ ክለብ ሀዲያ ሆሳዕና ከሰንጠረዡ ግርጌ በመላቀቅ ወደ መልካም ጎዳና ለማምራት ከነገው ጨዋታ የግድ ሙሉ ሦስት ነጥቦች ማሳካት ይኖርበታል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡና 5-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም የኋላ ኋላ መዳከሙና በቀላሉ ግቦች ሲቆጠሩበት መስተዋሉ በነገው ጨዋታም ሊቸገር እንደሚችል የሚጠቁም ነው። በተለይም ፈጣን ያልሆነውና ለጥቃቶች በቶሎ ምላሽ የማይሰጠው የተከላካይ መስመር ነገ ከበራሪዎቹ የሲዳማ ቡና አጥቂዎች ጋር የሚገጥመው ፉክክር ከባድ እንደሚሆን ይገመታል።

ሆሳዕና በአንፃሪዊነት ጥሩ የሆነበት የአየር ኳሶች አጠቃቀም ምናልባትም በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ለማሳካት ቁልፍ መሳርያ ሊሆናቸው ይችላል። በተለይ ተጋጣሚው ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ጨዋታዎች ሲስተዋሉባቸው የተስተዋሉ የመከላከል ድክመቶች በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ነገ ጥሩ ቀን ሊያሳልፉ ይችላሉ። ከዚህ ባሻገር በአማካይ ስፍራ ላይ ያላቸው የታታሪነት ባህርይ በጨዋታው የሲዳማን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንዲገቱ ያግዛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሆሳዕና በነገው ጨዋታ የበረከት ወልደዮሐንስን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን መሐመድ ናስርን ከጉዳት መልስ አግኝቷል።

ወጣ ገባ አቋም እያሳየ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ወደ ሰንጠረዡ አናት ፉክክር ለመመለስ የሚረዳውን ድል ለማግኘት አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

ከሜዳው ውጪ በሚያደርገው የነገው ጨዋታ የመልሶ ማጥቃትን ምርጫው አድርጎ እንደሚገባ የሚጠበቀው ሲዳማ ቡና በርካታ ጎሎችን በቀላሉ እያስተናገደ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን የተከላካይ መስመር በረጅሙ በሚጣሉ እና በመስመር በኩል በሚሻገሩ ኳሶች እንደሚፈትኑ ይጠበቃል።

በነገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በረጅም ጊዜ ጉዳት ከሜዳ ከራቀው ሚሊዮን ሰለሞን ውጪ የተሟላ ስብስቡን ይዞ ይገባል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ከ4 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይጫወታሉ። በ2008 ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሆሳዕና ላይ 1-1 ሲለያዩ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

አቤር ኦቮኖ

ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – አዩብ በቃታ

ሱራፌል ዳንኤል – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – አብዱልሰመድ አሊ – ሄኖክ አርፊጮ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ብርሀኑ አሻሞ – አበባየው ዮሀንስ

አዲስ ግደይ – ዳዊት ተፈራ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ይገዙ ቦጋለ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ