ቅድመ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ አዳማ ከተማ

መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማን የሚያገናኘውን የነገ 09:00 ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኋላ በፈረሰኞቹ ተሸንፈው ሊጉን የመምራት ዕድላቸውን ያባከኑት ምዓም አናብስት በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ ካገኙ በኃላ ለተከታታይ ጨዋታዎች ወጥ በሆነ የተጫዋቾች ምርጫ እና አደራደር ጨዋታዎቻቸው ያደረጉት መቐለዎች በነገው ጨዋታም በሁሉም ረገድ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በተለይም ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ ለውጦቹ የታዩበት የቡድኑ የማጥቃት ጥምረት ለግዙፎቹ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ በአንፃሩ ቡድኑ በፈጣኖቹ የአዳማ ከተማ አጥቂዎች መፈተኑ አይቀሪ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በሊጉ መጀመርያ አከባቢ ፈጣን አጥቂዎች ካላቸው ክለቦች ሲገጥሙ የተከላካይ ጥምረታቸው ላይ ለውጥ ያደረጉት መቐለዎች ከኋላ መስመር አሌክስ ተሰማ እና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ወደ ተቀያሪ ወንበር የወረደው አሚን ነስሩን የሚያጣምሩበት ዕድል እንዳለ ይታመናል።

መቐለዎች በነገው ጨዋታ ሚካኤል ደስታን በጉዳት አንተነህ ገ/ክርስቶስን በቅጣት አያሰልፉም።

በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን አቻ የተለያዩት እና በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታም በሜዳቸው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ የተጋሩት አዳማ ከተማዎች ከአንድ ሳምንት በኋላ በድጋሚ ወደ መቐለ አምርተው መቐለ 70 እንደርታን የሚገጥሙበት ጨዋታ ለቡድኑ ወሳኝ ነው።

ባለፉት ጨዋታዎች ከኋላ በሦስት እና በአራት የተከላካዮች ጥምረት የሚቀያየር አጨዋወት ይዘው የገቡት አዳማዎች ነገም እንደ ወትሮው በሶስቱ ፈጣን አጥቂዎቻቸው መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ከተጋጣምያቸው አጥቂዎች አንፃር ሲታይ በፍጥነት ዝግ ያሉት የአዳማ ተከላካዮች በዚ ጨዋታ የተለየ አቀራረብ እና ቅርፅ ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አዳማ ከተማዎች በነገው ጨዋታ ሚካኤል ጆርጅ እና ብሩክ ቃልቦሬን በጉዳት ምክንትያት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ ሁለቱን ሲያሸንፍ አዳማ አንዱን አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። መቐለ 6፣ አዳማ 5 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አስናቀ ሞገስ

ዮናስ ገረመው – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሱ – ያሬድ ከበደ

ኦኪኪ ኦፎላቢ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

አዳማ ከተማ (3-5-2)

ጃኮ ፔንዜ

መናፍ ዐወል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ

ፉአድ ፈረጃ – አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ቡልቻ ሹራ – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ