ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም የሚደረገው የሃዋሳ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታን በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድን ከሦስት ጨዋታዎች በፊት (በ3ኛ ሳምንት ባህር ዳርን 1-0 ያሸነፈበት) ያስመዘገበውን ሦስት ነጥብ ዳግም በደጋፊው ፊት ለመድገም ነገን ይጠባበቃል። ከሁለት አስከፊ ሽንፈቶች (በኢትዮጵያ ቡና4-1 እና በሲዳማ ቡና 3-1) በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል አምርቶ ከሊጉ ጠንካራ ቡድን (ወልዋሎ) ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ቀስ በቀስ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባል።

የሁለቱ አጥቂዎች መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ፍጥነት እንደ ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ እየተጠቀመ የሚገኘው ቡድኑ በነገው ጨዋታም ሁለቱን ያማከለ አጨዋወት እንደሚከተል ይጠበቃል። አሰልጣኙ ሁለቱ ተጨዋቾችን ካማከለ አጨዋወት በዘለለ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ልምምድ የጀመረው ግዙፉ አጥቂ እስራኤል እሸቱን በቋሚነት የሚጠቀም ከሆነም ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶች ምርጫው እንደሚያደርግ ይገመታል።

ባለፈው ሳምንት የወልዋሎ የማጥቃት አጨዋወት ለመመከት ያልተቸገሩት የሀይቆቹ ተከላካዮች በነገው ዕለት በሳልሀዲን እና ጌታነህ ጥምረት ይፈተናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለሜዳዎቹ በነገው ጨዋታ የቸርነት አውሽን ግልጋሎት እንደማያገኙ ተነግሯል።

ተጋባዦቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ከሦስት ቀናት በፊት ያስመዘገቡትን ጣፋጭ ድል ዳግም ለማጣጣም እና ህዳር 30 ከተደረገው የሰበታ ጨዋታ በኋላ የተገኘውን የማሸነፍ መንገድ ለማስቀጠል ወደ ሀዋሳ አምርተዋል።

ጎሎችን የማስቆጠር ችግር ያለበት ቡድኑ በመቐለው ጨዋታ ችግሮቹ በመጠኑ የተፈቱ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ አንጋፋው እና አይምሬው አጥቂ ሳልሃዲን ሰዒድ ከጉዳት መመለሱ የፊት መስመሩን እጅግ አጠናክሮታል። የሳልሃዲን ብቻ ሳይሆን የጌታነህ እና የአቤል ጥምረትም ወደ ጥሩ ውህደት (chemistry) የመጣ በመሆኑ ለቡድኑ ጥሩ ነገርን ያመጣል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ነገ ከጨዋታ ጨዋታ እየተፍረከረከ የመጣውን የሃዋሳ የተከላካይ ክፍል እንዲፈተን ያደርገዋል።

ከቡድኑ የፊት መስመር በተጨማሪ የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹ( ሙላለም እና ሃይደር) ወደ ጥሩ ብቃት መምጣት ቡድኑን ሊጠቅም ይችላል። ከሁለቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ ከመስመር እየተነሳ ጥቃቶችን የሚያስጀምረው ጋዲሳ ብቃት በነገው ጨዋታ ለተጋጣሚ አደጋ ነው።

አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጂኖቭ አቡበከር ሳኒን ከጉዳት መልስ ሙሉ ለሙሉ ሲያገኙ በአስተማማኝ ሁኔታ ያላገገመው ናትናኤል ዘለቀን ምናልባት ላይጠቀሙበት እንደሚችል ተገምቷል። ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው ለዓለም ብርሀኑ አሁንም ለጨዋታ ብቁ ባለመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 40 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 24 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 67 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 31 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት በድምሩ 98 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ምናልባትም በነገው ጨዋታ መጠኑ ወደ 100 እንደሚደፍን ይጠበቃል።

– ዐምና ሁለቱንም ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሃዋሳ ከተማ (4-4-2)

ቤሊንጌ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ኩዋሜ ኦሊቨር

ፀጋአብ ዮሐንስ – ተስፋዬ መላኩ – አለልኝ አዘነ – ሄኖክ ድልቢ

ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-4-2)

ፓትሪክ ማታሲ

ደስታ ደሙ – ኤድዊን ሪምፖንግ – አስቻለው ታመነ – ሄኖክ አዱኛ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ – ሳልሃዲን ሰዒድ


© ሶከር ኢትዮጵያ