ጅማ አባጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት የ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ከሜዳ ውጪ ባሉ ነገሮች (የደሞዝ ጉዳይ) ተወጥሮ የሰነበተው ጅማ አባጅፋር ነገ ሁለተኛ የሜዳ ላይ ድሉን ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል። ባሳለፍነው ሳምንት ካለ መደበኛ ልምምዶች ወደ አዳማ አቅንቶ ነጥብ ይዞ የተመለሰው ቡድኑ አሁንም አስተዳደራዊ ችግሮች እንዳሉበት ተነግሯል። በአበበ ቢቂላ ስታዲየሙ ጨዋታ ሁለት መልኮችን ያስመለከተው ጅማ በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው ወልቂጤ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እንደሚኖረው ይጠበቃል። ለዚህም ደግሞ ሰፊ የሜዳ ክፍሎችን ማካለል የሚችሉ ተጫዋቾች ቡድኑ በመያዙ በነገው ጨዋታ ከወልቂጤ በተሻለ የመሃል ሜዳ ብልጫ እንደሚኖረው እንዲገመት አስችሎታል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ምንም ልምምድ ሳይሰራ ወደ አዳማ አቅንቶ የነበረው ቡድኑ ለነገው ጨዋታ ሦስት የልምምድ መርሃ ግብሮችን እንዳከናወነ ተገልጿል። ምንም እንኳን እስካሁን የተጨዋቾቹ የደሞዝ ጥያቄ ምላሸ ባያገኘም የውጪ ዜጎቹ ተጨዋቾች ጉዳይ በከፊሉ ተፈቷል። ቡድኑ ካስፈረማቸው ሦስት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች መካከልም አጥቂው ያኩቡ መሐመድ እና ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ የነበረባቸው የፓስፖርት ችግር ተፈቶላቸው ለነገው ጨዋታ ብቁ እንደሆኑ ተነግሯል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ከተጨዋቾቹ ታታሪነትን ለሚሻው ጳውሎስ ጌታቸው ተጨማሪ አማራጮችን በመስጠት ለጨዋታው እንዲቀርብ ያደርገዋል። በተለይ እስካሁን ምንም ጨዋታ ለቡድኑ ያልተጫወተው ያኩቡ ስልነት ያጣውን የፊት መስመር ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በባለሜዳዎቹ በኩል በዘንድሮ የውድድር ዓመት ክስተት የሆነው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ተነግሯል። ነገር ግን በዚህ ቦታ ላይ ቡድኑ ዘሪሁን ታደለ እና መሐመድ ሙንታሪ እንደ አማራጭ በመያዙ በጨዋታው ይጎዳል ተብሎ አይጠበቅም። ከሰዒድ በተጨማሪ ሄኖክ ገምቴሳ እና ብሩክ ገብረአብ በጨዋታው እንደማይኖሩ ተጠቁሟል።
በአሰልጣኝ ደግአረገ የሚሰለጥኑት ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ደረጃ ሰንጠረዥ አናት ለመቅረብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘው አዲሱ የሊጉ ክልብ ወልቂጤ በነገው ጨዋታ ጥንቃቄን መርጦ እንደሚጫወት ይታሰባል። እርግጥ ቡድኑ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ቦታን ቢሰጥም ጅማ ካለው የሜዳው ላይ ጥንካሬ አንፃር ወደ ኋላ እንደሚያፈገፍግ ይገመታል።
ከስሑል ሽረ ጋር በተደረገ የ6ኛ ሳምንትም የሊጉ መርሃ ግብር ጎል ለማስቆጠር ተፈትኖ የነበረው ቡድኑ የሜዳውን መስመር ለመጠቀም በመገደድ የመስመር አጨዋወቱን አጠናክሮ ሲቀጥል ታይቷል። በዚህም በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች የቡድኑ የመስመር ተጨዋቾች ተጋጣሚን ሲያስጨንቁ ተስተውሏል። በነገውም ጨዋታ ጅማ ካለው ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት አንፃር ይህ አጨዋወት የቡድኑ መለያ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህም በተጨማሪ አማካዩቹ ወደ ፊት በመጠጋት የአጥቂ ክፍሉን በይበልጥ ሊያግዙ እና የዘገዩ ሩጫዎችን በማድረግ የቡድኑን ሁነኛ አጥቂ ጃኮ አራፋትን እንደሚያግዙ ይጠበቃል።
ቡድኑ ቶማስ ስምረቱ፣ ፍፁም ተፈሪ፣ በቃሉ ገነነ እና አዳነ አባይነህ በነገው ጨዋታ እንደማያሰልፍ ተጠቁሟል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በነገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)
መሐመድ ሙንታሪ
ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ
ኤፍሬም ጌታቸው – ንጋቱ ገ/ሥላሴ
ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አህመድ – አምረላ ደልታታ
ያኩቡ መሐመድ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ይድነቃቸው ኪዳኔ
ይበልጣል ሽባባው – ዐወል አህመድ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዘር ኦቴ
ኤፍሬም ዘካሪያስ – በረከት ጥጋቡ – አብዱልከሪም ወርቁ
ሄኖክ አወቀ – ጃኮ አራፋት – ጫላ ተሺታ
© ሶከር ኢትዮጵያ