ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን የሚጋብዝበትን ጨዋታ የዳሰሳችን ማሳረጊያ አድርገነዋል።

በሊጉ ጥሩ አጀማመር ያደረገው ባህር ዳር ከተማ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ያጣውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል። በተለይ በ6ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ወደ ጎንደር አምርቶ ሦስት ነጥብ እና ሶስት ጎል አስረክቦ የመጣው ቡድኑ በጨዋታው ላይ የነበረውን የእንቅስቃሴ የበላይነት ለማስቀጠል እና የጨዋታ የበላይነቱን በውጤት ለማጀብ 9 ሰዓትን ይጠባበቃል።

በፋሲሉ ጨዋታ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ ፍጥነትን እና ቀጥተኝነት ላይ እንደሚያዘነብሉ ይገመታል። ምክንያቱም የተጋጣሚያቸው (ኢትዮጵያ ቡና) የጨዋታ ዘይቤ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ቡድኑ በተወሰነ መልኩ ኳስን ለቆ እንደሚጫወት እንዲገመት አድርጎታል። በዚህ የጨዋታ ሂደት ደግሞ ቡናማዎቹ ኳስን ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ለመመስረት ስለሚጥሩ ባህር ዳሮች በፍጥነት አስጨንቀው (ፕሬስ አድርገው) ገና የኳስ ሂደቱ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሳይሸጋገር አደጋዎችን እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል። ከዚህ ውጪ አጥብቦ የሚጫወተውን የቡና የአማካኝ መስመር በልጦ ለመገኘት ቡድኑ የመስመር አጨዋወቱን አጠናክሮ እንደሚገባ ይጠበቃል። ነገር ግን በዚህ የመስመር አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ የሆነው ወሰኑ ዓሊ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ስለሆነ መቀዛቀዞች እንዳይኖሩ አስግቷል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በቆሙ ኳሶች አደገኛነቱ እየታየ ያለው ባህር ዳር ከተማ በነገው ጨዋታም የአየር ላይ አጋጣሚዎችን በማሸነፍ የግብ እድሎችን እንደሚፈጥር ይገመታል። ለዚህ ደግሞ በደሞዝ ምክንያት የፋሲሉ ጨዋታ ያመለጣቸው ማማዱ ሲዲቤ እና አዳማ ሲሶኮ ወደ ስብስቡ ስለተካተቱ ባህርዳሮች ሊጠቀሙ ይችላሉ። ነገር ግን ቡድኑ ያለበት የጎል ማስተናገድ አባዜ ነገም ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል። በተለይ ደግሞ ሦስቱ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂዎች ፍጥነታቸውን ተጠቅመው ይህንን አስተማማኝ ያልሆነውን የተከላካይ መስመር እንደሚረብሹ እንዲታሰብ ያደርጋል።

በባህር ዳር በኩል በ6 የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው ወሰኑ ዓሊ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው።

በሜዳቸው እጅግ አስፈሪ እየሆኑ የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሜዳቸው ውጪ ያለባቸውን አይናፋርነት ለመቅረፍ እና በአሸናፊነት ለመዝለቅ ወደ ባህር ዳር አምርተዋል። ከአራት ቀናት በፊት ሃዲያ ሆሳዕና ላይ አምስት ግቦችን ያስቆጠሩት ቡናማዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ለማስመስከር ለጨዋታው ይቀርባሉ።

በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚሰለጥነው ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደሚፈለገው መንገድ እየገባ ይመስላል። በተለይ አላማ ያላቸውን የጎንዮሽ እና የፊትዮሽ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ ለመድረስ የሚሞክርበት መንገድ እየተሻሻለ መጥቷል። ከእነዚህ የኳስ ቅብብሎሽ በተጨማሪ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች የቡድኑ የልብ ምት እየሆኑ መጥቷል። በነገው ጨዋታም እነዚህ የመስመር አጥቂዎች ለቡድኑ ዋነኛ አጥቂ እንዳለ ደባልቄ ኳሶችን ከማመቻቸት ባለፈ ሰብረው በመግባት ተጋጣሚን እንደሚያስደነግጡ ይገመታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የማይቸገረው ቡድኑ አጋጣሚዎችን ፍሬያማ የማድረግ ክፍተት አለበት። ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታ (ሀዲያ ሆሳዕና) ብቻ በርከት ያሉ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሲያመክን የታየው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ይህንን ችግር ካልቀረፈ ሊቸገር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከመስመር የሚነሱ የአየር ላይ ተሻጋሪ ኳሶችን በአግባቡ ካልመከተ ሊጎዳ ይችላል።

በቡድኑ በኩል አሁንም ታፈሰ ሰለሞን ለጨዋታ ዝግጁ ባለመሆኑ ወደ ባህር ዳር እንዳላቀና ተነግሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት ዐምና ሲሆን አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና 5-0 ፣ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊ ሆነዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሃሪስተን ሄሱ

ሳላምላክ ተገኝ – አቤል ውዱ – አዳማ ሲሶኮ – ሚኪያስ ግርማ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ -ሳምሶን ጥላሁን

ግርማ ዲሳሳ – ማማዱ ሲዲቤ – ፍቃዱ ወርቁ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገ/ተንሳይ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አስራት ቱንጆ

ፍ/የሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሣ – አማኑኤል ዮሐንስ

አቤል ከበደ – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር


© ሶከር ኢትዮጵያ