ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

በኢትዮጵያ ሆቴል ዛሬ ከሰዓት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ቡድኑ የዝግጅት ጊዜ እና ስለ ተጨዋቾች አመራረጥ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን መግለጫ በኋላ የተከናወነውን ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል እና የቡድኑ አምበል እመቤት አዲሱ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል ሃሳቡን ለጋዜጠኞች አካፍሏል። “ለሴቶች እግርኳስ እና ለሴቶች ሊግ ቀረብ ያልኩኝ ስለሆንኩ በተሻለ ደረጃ ያሉትን ተጨዋቾች ለመመልከት እና ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ልምምድ ከጀመርን አምስት ቀናት ተቆጥረዋል። በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዶችን እየሰራ ነው። ባለችን ቀን ውስጥ በአካል ብቃት እና በታክቲክ በጥሩ ሁኔታ ለመዘጋጀት ሞክረናል። በአብዛኛው ግን ተጨዋቾቹ ከዝግጅት ስለመጡ ታክቲካዊ ስራዎች ላይ አተኩረናል። በአጠቃላይ አብረውኝ ከተመደቡ ባለሙያዎች ጋር ሆነን ተጨዋቾቹን ወደ ጨዋታ ስሜት ለማምጣት እየሰራን ነው።” ብለዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው ሃሳቡን ካካፈለ በኋላ የቡድኑ አምበል እመቤት አዲሱ የሚከተለውን ብላለች።

“ቡድኑ ልምድ ያላቸውንም ልምድ የሌላቸውን ተጨዋች አካቷል። ያለን ጊዜም አጭር ከመሆኑ የተነሳ የቅንጅት ስራዎች ካይ ትኩረት አድርገን ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን። የቡድኑ ስሜትም በጣም ደስ ይላል። አብዛኛው ተጨዋች ገና ታዳጊ ስለሆነ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ይሞክራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ግብዓት ለመሆንም ስለሚጥሩ የተሻለ ነገር ይሰራሉ። ከዝግጅት እና ከጨዋታ ስለመጣን የአካላዊ ብቃት አይከብደንም ብዬ አስባለሁ።”

ከሁለቱ የቡድኑ አባላት ንግግር በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች በቦታው ከተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።

ስለ ዝግጅት ጊዜ አጭርነት?

በስድስት ቀን ዝግጅት ብሄራዊ ቡድን መገንባት ከባድ ነው። እርግጥ እስከ ጨዋታው ቀን ድረስ 10 ቀናት አሉን። በእነዚህ ቀናት የተሻሉ ነገሮችን ለመስራት እንጥራለን። ከምንም በላይ ደግሞ ተጨዋቾቹ ከዝግጅት እና ውድድር ስለመጡ የአካል ብቃት ደረጃቸው የተሻለ እንደሚሆን አስባለሁ። ተጨዋቾችንም ስንመርጥ ታክቲካሊ ዲስፕሊን የሆኑ ተጨዋቾችን ስለመረጥን የምንቸገር አይመስለኝም። በአጠቃላይ ግን በሳይኮሎጂ እና ታክቲካዊ ነገሮች ተጨዋቾቻችንን ባለን አጭር ጊዜ ለማብቃት እየሞከርን ነው።
ስለ ቡድኑ ጠንካራ ጎን?

ቡድኑ መሰረቱን ጠብቆ የመጣ ቡድን ነው የሚል እምነት የለኝም። በየጊዜው አዲስ ቡድን ነው ለመገንባት እየተጣረ ያለው። አሁን እኔ እያረኩ ያለሁት ቡድኑን የማዋቀር ስራ ነው። ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን በጥቂቱ ነገርግን ልምድ የሌላቸው ተጨዋቾችን በደንብ ወደ ስብስቡ ለመክተት ሞክረናል። ከምንም በላይ ግን የመረጥኳቸው ተጨዋቾች ሃገርን ወክለው ሊጫወቱ ስለሆነ ጠንካራ ጉንን በራሳቸው ያዳብራሉ ብዬ አስባለሁ።

ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኙ ስላስቀመጠው ሃላፊነት እና እቅድ…?

ማንኛውም ሰው ቡድን ሲሰጠው ውጤታማ አድርግ ተብሎ ነው። ፌደሬሽኑ ግን ጥሩ ቡድን እንድገነባ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እድል ያላገኙ ተጨዋቾችን ይዤ መሰረት ያለው ነገር እንድጥል ሃላፊነት ተሰጥቶኛል። በግሌ ደግሞ ከፊቴ ያለውን የብሩንዲ ጨዋታ በቅድሚያ የማሸነፍ እቅድ አለኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ