የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 3-2 ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት መርሀግብር ባህር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።
👉 ” ለተጋጣሚያችን መጫወቻ ቦታ ሰጥተን ራሳችን ላይ አደጋ ጋብዘናል” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለጨዋታው

ባለፈው ጨዋታችን ተሸንፈን እንደመምጣታችን ከዛ ስሜት ተሎ ይሄን ጨዋታ በማሸነፍ መውጣት እንፈልግ ነበር፤ ተሳክቶልናል። ጨዋታውን አሸንፈን ደጋፊዎቻችን ተደስተው ከስታዲየም ስለወጡ ደስ ብሎኛል። ወደ ጨዋታው ስመለስ በመጀመሪያው አጋማሽ ባቀድነው ባሰብነው መንገድ ተጫውተናል፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ምንም እንኳን ጨዋታውን ብናሸንፍም በእንቅስቃሴችን ደስተኛ አይደለሁም። ለተጋጣሚያችን መጫወቻ ቦታ ሰጠን ራሳችን ላይ አደጋ ጋብዘናል። ያው ግን ከመሸነፍ የመጣ ቡድን አንድ አንድ ጊዜ ያለው የስነልቦና ዝግጅት ጨዋታውን ማሸነፍ ስለሆነ ተጫዋቾቼ ግባቸውን ማስጠበቅ እንጂ በመጫወት ምናገኘውን ጥቅም ወደ መጨረሻ ላይ ስላልተረዱ ጫና ውስጥ ገብተን ነበር።

ለሁሉም አስፈላጊውን ነጥብ አግንተናል፤ ተጋጣሚያችን ባለፈው በተከታታይ በነበረው ጨዋታ በጥሩ ውጤት እያሸነፈ ስለመጣ ከኛ የተሻላ ስነልቦና ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ ያን መስበር እና ቡና በጣም ፖሰስ የሚያደርግ ቡድን ስለሆነ የበለጠ በራስ መተማመናቸውን ከፍ አድርገው እንዳይጫወቱ ጨዋታውን አስቸጋሪ ለማድረግ ሞክረን ተሳክቶልናል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ደስተኛ አይደለንም።

የውጪ ተጫዋቾቹ ተፅዕኖ

ግለሰቦችን ነጥዬ ማየት አልፈልግም! እኔ ቡድን ነው እየሰራሁ ያለሁት! በቡድኔ ውስጥ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ተጫዎቾች ይኖራሉ። ከፋሲል ጋር የነበረን ጨዋታ ካያችሁት እንቅስቃሴው ውጤቱን አይገልፅም። የተሻልን ነበርን፤ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ የጥራት ችግር ስለነበረብን ግን ጎሎችን ማግባት አልቻልንም። ግን የግለሰቦችን ስም ጠርቼ ማውራት አልፈልግም። ምክንያቱም ባህር ዳር እንደ ቡድን የሚጫወት ጠንካራ ቡድን እንዲኖረው ነው የምፈልገው።


👉 ” ነጥብ ይዘን መውጣት ነበረብን ብዬ አስባለሁ” ካሣዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነው፤ ነጥብ ይዘን መውጣት ነበረብን ብዬ አስባለሁ። ከእረፍት በፊት የተቆጠሩ ግቦች ስንጫወት ከፍተን ስለምንጫወት ሁልጊዜ ተጋጣሚ ሲነጥቅ የተከፈቱ ቦታዎችን ያገኛል። ስለዚህ እነዛን ቦታዎች ቶሎ ያለመዝጋት ጉዳይ ነው ግቦች የተቆጠሩብን። ከዛ በኋላ እንግዲህ ምናልባት የግቡ መብዛት ልጆቹን እንዳይረብሻቸው አንድ የሆነ ነገር ማድረግ ነበረብን። ከእረፍት በኋላ የነበረው እንቅስቀሴ ጥሩ ነበር፤ የባከኑ ኳሶች ነበሩ። ምናልባት እነዛ ወደግብ ቢቆጠሩ ነጥቡን ይዘን መውጣት እንችል ነበር ብዬ ነው የማስበው። ጥሩ ነው ጨዋታው እንዳጠቃላይ ።

በቡና እና በተጋጣሚያቸው መካከል ሜዳ ላይ
የነበረው ልዩነት..

ሜዳ ላይ የነበረው ልዩነት እነሱ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው ነጥቀው የተከፈቱ ቦታዎችን ነው የሚጠብቁት። እነሱ አላማ አድርገው ያነን ነው ሲያደርጉ የነበረው። እኛ ደግሞ የራሳችንን ኳስ መስርተን ለመጫወት ነው የምንፈልገው። እንዳልኩት እንግዲህ ያንን አላማ አድርገው የሚጫወቱት የሆነ ቦታ ላይ እስክንገባላቸው ነው የሚጠብቁት። እዛ ቦታ ላይ ስንገባ ኳሱን አስጥለው በመልሶ መጥቃት ግብ ማስቆጠር ነው የሚፈልጉት። ሁለተኛው አጋማሽም ከዛ የተለየ ነገር አልነበረም። እኛ እንዲያውም ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ቁጥራችን አንሷል። ምናልባት እነሱም ያንን ውጤት ማስጠበቅ ስለፈለጉ ይመስላል አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ወደ ኋላ ተመልሰው ይጫወቱ ነበር።

ብዙ ግብ ማስቆጠር እና ማስተናገድ

በሆኑ አጋጣሚዎች ግብ ልታስቆጥር ትችላለህ፤ መመዘን ያለበት ግን አጠቃለይ ያለው እንቅስቃሴ ነው። አስተማማኝ የሚሆነው የምታገባቸው ግቦች ሳይሆን በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ተጋጣሚህ ላይ የነበረው የበላይነት ነው። አንድ ለዜሮም አሸንፈህ የበላይነቱ ካለ በሚቀጥለውም ማሸነፍ ትችላለህ። ስድስት ሰባትም አግብተህ የበላይነቱ ከሌለ ያንን ውጤት አስጠብቀህ መሄዱ ከባድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ብዙ ትኩረት የምናደርገው እንቅስቃሴው ላይ ነው። አጨዋወቱ ምን ይመስላል ነው፤ ግጥሚያውን የመቆጣጠር ሂደቱ ምን ይመስላል የሚለውን ነው። ከዛ አንፃር ሲታይ ዛሬ ጥሩ ነበርን ብዬ ነው የማስበው ።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ