በሰባተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 3-2 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል ።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ባለሜዳው ክለብ ለኢትዮጵያ ቡና የሁለቱ ቡድኖች አርማ ያለበት የፎቶ ፍሬም ስጦታ ያበረከተ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለባህር ዳር ከተማ ለተጫወቱት ወንድሜነህ ደረጀ እና እንዳለ ደባልቄም ምስላቸውን የያዙ የፎቶ ፎሬሞች አበርክተዋል።
በባለሜዳዎቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በደሞዝ ጥያቄ ምክንያት ከስብስቡ ውጭ የነበሩት የውጪ ዜጎቹ ሀሪስተን ሄሱ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አዳማ ሲሶኮ ወደ ስብስቡ ተመልሰው ፅዮን መርዕድ፣ ስንታየሁ መንግስቱ፣ ወሰኑ አሊ ወደ ተጠባባቂነት ሲወርዱ ዳንኤል ኃይሉም በፍቅረሚካኤል ዓለሙ ምትክ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በእንግዳዎቹ በኩል ሀዲያ ሆሳዕናን 5-0 ካሸነፈው ስብስብ እንዳለ ደባልቄን በሀብታሙ ታደሰን ብቻ ለውጥ በማድረግ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት ።
ባህር ዳሮች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኟቸውን ኳሶች በአግባቡ በተጠቀሙበት የመጀመሪያው አጋማሽ 3 ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በሙከራ ደረጃ በ13ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ግርማ ደሲሳ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ነበር። እንግዶቹ በበኩላቸው አቡበከር ናስር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ሲያድንበት በ5ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሳጥን ውስጥ ከሀብታሙ ታደሰ የተሰጠውን ጥሩ ኳስ አቡበከር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ የጨዋታውን ቅርፅ ሊለውጥ የሚችል አጋጣሚ ነበር።
ቡናማዎቹ ኳሱን ተቆጣጥረው በሚጫወቱበት አጋጣሚ የሚገኙ ስህተቶች በቀጥታ በመልሶ ማጥቃት በጥቂት ኳስ ንክኪ ወደ ራሳቸው ግብ ክልል እየደረሱ ግቦች ተቆጥረውባቸዋል። 14ኛው ደቂቃ ላይም ዳንኤል ኃይሉ ከሳጥን ውጪ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ አርፎ የጣናው ሞገድ ከጅምሩ መሪ እንዲሆን አስችሏል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ማማዱ ሲዲቤ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ግርማ ሳጥን ውስጥ በመግባት ለፍፁም ዓለሙ አሻግሮለት ፍፁም ወደግብ ቀይሮ የባህር ዳርን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል።
በጊዜ ጎሎች ያስተናገዱት ቡናዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምአንተ ካሣ ከሳጥን ውጭ ወደግብ አክርሮ በመታው ኳስ አፀፋ ለመስጠት ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀርቷል። ብዙም ሳይቆይ ማማዱ ሲዲቤ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠበቂው በረከት በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ፍፁም ዓለሙ አግኝቶ ወደ ግብ በመቀየር መሪነታቸውን ወደ ሦስት አስፍቷል።
ከባህር ዳር ተከታታይ ጎሎች በኋላ በቀሩት የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር፤ ባህር ዳሮች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የሚጠቀሱ የጎል ሙከራዎች የታዩት ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ነበር። በጣናው ሞገድ በኩል 44 ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ሲዲቤ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ ሲሆን በቡና በኩል 41ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ማግኘት ችለዋል። አማኑኤል ዮሐንስ ላይ በተሰራ ጥፋት ግማሽ ጨረቃው ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት አቡበክር ናስር በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሮ ልዩነቱን አጥብቧል።
ከጎሉ በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ቡናዎች 44ኛው ላይ አቡበከር ናስር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በቀላሉ ያመከነውና በቀኝ መስመር አቤል ከበደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ወደ ግብ ሞክሮ ሀሪስተን ያዳናቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ ክፍተታቸውን በመድፈን አስፈሪ ሆነው የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የባህር ዳር ስታዲየም ምቹነትን በመጠቀም ኳስን በአግባቡ በማንሸራሸርና የጎል አጋጣሚዎችን በመፍጠር የበላይነት አሳይተዋል።
በ53ኛው ደቂቃ አቤል ከበደን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቁጥር መጉደላቸው ሳይበግራቸው 69ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ ነፃ ለነበረው ፍቅረየሱስ በማመቻቸት አማካዩ ወደ ግብ ቀይሮት ልዩነቱን ወደ አንድ አጥብቧል።
በጎሉ ይበልጥ የተነቃቁት ቡናማዎቹ አቻ ለመሆን ያቃረቧቸውን ተደጋጋሚ ሙከራቸዎች አድርገዋል። በተለይ በ74ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ሀብታሙ ታደለ ያሻገረውን ድንቅ ኳስ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም በተከላካዮች ተጨርፎ የወጣበት እንዲሁም ጨዋታው ላይ ደምቆ የዋለው አቡበክር ናስር 76ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሽድ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ቀጥታ ወደግብ መትቶ ሀሪስተን ሄሱ ያዳነበት፤ በተጨማሪም በ86ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ውጪ መትቶ ግብ ጠባቂው በድጋሚ የያዘበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
በአጋማሹ የተዳከሙት በባለሜዳዎቹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ አፈግፍገው የተጫወቱ ሲሆን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉትም በመልሶ ማጥቃት 75ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ደሲሳ በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ አንድ ተከላካይ አልፎ በቀጥታ ወደግብ የመታውና ግብ ጠባቂ በቀላሉ ያዳነበት ብቻ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ በ11 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በ9 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ